ክርስትያኖ ሮናልዶና ማንችስተር ዩናይትድ በስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ ይፋ አደረገ
ፓርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ "ተከድቻለሁ" ማለቱ ይታወሳል
ሮናልዶ በማንችስተር ዩናይትድ ቆይታውበ346 ጨዋታዎች 145 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል
ክርስትያኖ ሮናልዶ እና ማንችስተር ዩናይትድ በስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ ይፋ አደረገ።
የ37 አመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ በቶክ ቲቪ ባደረገው ሰፊ ቃለ ምልልስ ከዩናይትድ እየተገፋ እንደሆነ እንደሚሰማው፣ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግን እንደማያከብር እና የግላዘር ቤተሰብ ለክለቡ ምንም ደንታ እንደሌለው መናገሩ አይዘነጋም።
የቃለ ምልልሱ ማጠንጠኛ በማንቸስተር ቤት የ"ተከድቻለሁ" አይነት ሲሆን ቃለ ምልልሱን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች በመጉረፍ ላይ መሆናቸውም ይታወቃል።
አስተያየቶቹ በአመዛኙ በሮናልዶ ላይ ያነጣጠሩና ፖርቹጋላዊው ኮከብ ራሱን ከክለብ በላይ አድርጎ ቆጥሯል የሚል ይዘት ያላቸው ናቸው።
በሮናልዶ ቃለ ምልልስ የተበሳጨው ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድም ቢሆን በተጫዋቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከቀናት በፊት አስታውቋል።
ክለቡ ባወጣው መግለጫ በተጫዋቹ ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ቢገልጽም ምን አይነት እርምጃ እንደሚወስድ ከመግለጽ ተቆጥቦ ነበር።
ማንችስተር ዩናይትድ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ በስምምነት ላይ በተመሰረተ መልኩ ኮንትራት ለማቋረጥ እና ለመለያየት መስማማታቸውን አስታውቋ።
ማንችስተር ዩናይትድ የ37 ዓመቱ ፖርቹጋላዊውአጥቂ ክርስትያኖ ሮናልዶ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ለክለቡ ለሰጠው ግልጋሎትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሮናልዶ በማንችስተር ዩናይትድ በቆየባቸው ጊዜያት በ346 ጨዋታዎች 145 ጎሎችን በማስቆጠር ከክለቡ ታላላቅ ተጫዋቾች በቀደሚነት የሚመደብ ነው።