ቴንሀግ በማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝነታቸው እንዲቀጥሉ የክለቡ ቦርድ ወሰነ
ሰር ጂም ራትክሊፍ ዩናይትድ የነበረበት ሁኔታ የአሰልጣኙን ሙሉ ብቃት ለመለካት አያስችልም ብለዋል
የክለቡን ውሳኔ መቀበላቸውን ያሳወቁት ቴንሀግ በማንችስተር ቤት በመቆየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል
የማንችስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ በሀላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ ክለቡ አስታውቋል፡፡
ክለቡ በ2023/24 የውድድር ዘመን ያሳለፈውን መጥፎ የውድድር አመት ተከትሎ አሰልጣኙ ከክለቡ ሊሰናበቱ እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል፡፡
የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን የቀያይ ሰይጣኖችን አፈጻጸም እና የአሰልጣኙን ሁኔታ ለሁለት ሳምንት የገመገመው የማንችስተር ዩናይትድ ቦርድ ቴንሀግ በክለቡ አሰልጣኝነታቸው እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡
የክለቡን 27.7 በመቶ ድርሻ የገዙት ሰር ጂም ራትክሊፍ ዩናይትድ በአጠቃላይ የነበረበት ሁኔታ የአሰልጣኙን ሙሉ አቅም ለመገምገም የሚያስችል አይደለም ነው ያሉት፡፡
በ11 አመታት ውስጥ በርካታ አሰልጣኞችን ቢቀይርም ስኬታማ መሆን አልቻለም ያሉት ራትክሊፍ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ራትክሊፍ የክለቡ ቡድን መዋቅር እና አስተዳደራዊ ሁኔታ በድጋሚ መፈተሸ ስላለበት ለተሄንሀግ ተጨማሪ እድል ለመስጠት ቦርዱ ውሳኔ ማሳለፉን ነው ይፋ ያደረጉት ፡፡
በታሪኩ አስከፊ የተባለውን የውድድር ዘመን ያሳለፈው ዩናይትድ በውድድር ዘመኑ 8ኛ ደረጃን ይዞ ቢያጠናቅቅም የኤፍኤካፕ ዋንጫን ማንሳት ችሏል፡፡
ከማንችስተር ዩናይትድ ውጤት መዋዠቅ ጋር ተያይዞ የአሰልጣኝ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ሲዘግቡ የቆዩት የእንግሊዝ ጋዜጦች የተለያዩ አሰልጣኞችን ከክለቡ ጋር አያይዘው ሲጽፉ ነበር፡፡
ጋሬዝ ሳውዝጌት፣ ግራሀም ፖተር፣ ቶማስ ቱኸል እና ማውሪሲዎ ፖቼቲኖ የዩናይትድ አለቃ እንደሚሆኑ ሲጠበቁ ከነበሩ አሰልጣኞች መካከል ይገኙበታል፡፡
ቴንሀግ የአሌክስ ፈርጉሰን መልቀቅን ተከትሎ ማንችስተርን በሀላፊነት ከያዙት ዴቪድ ሞይስ፣ ልዊስ ቫንሃል፣ ጆዜ ሞሪኒሆ እና ኦሊጉነር ሶልሻየር ቀጥሎ ክለቡን በቋሚ አሰልጣኝት የመሩ አምስተኛው ሰው ናቸው፡፡
በ2022 የውድድር ዘመን ማንችስተርን የተረከቡት የ54 አመቱ ኔዘርላንዳዊ አሰልጣኝ በመጀመርያ የውድድር ዘመናቸው ዩናይትድ በፕርሚየርሊጉ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን የኤፍ ኤካፕ ፍጻሜ ደርሶ በሲቲ ሲሸነፍ፣ የካራባዎ ዋንጫን ደግሞ ማንሳት ችሏል፡፡
በ2023/24 የውድድር ዘመን ጅማሬው ያላማረው ዩናይትድ በሊጉ መጀመርያ ካደረጋቸው የመጀመርያ አስር ጨዋታዎች ስድስቱን ተሸንፏል፡፡
የቴንሀግን መቀጠል ያረጋገጠው ማንችስተር ዩናይትድ በሚቀጥለው ወድድር አመት ውላቸው የሚጠናቀቀውን አሰልጣኝ ውል በሚያራዝምበት ሁኔታ ላይ እየመከረ ይገኛል፡፡