ፕሪሚየር ሊጉ ሳይጀመር ተደጋጋሚ ጉዳቶችን እያስተናገደ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ
ቡድኑ በትላንትናው እለት ከሪያል ቤቲስ ጋር ባደረገው ጨዋታ ተጨማሪ ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹ ተጎድተውበታል
ኤሪክ ቴንሀግ የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት የቡድኑን ጥልቀት የሚጠናክሩ ተጫዋቾችን ማስፈረም ካልተቻለ የውጤት ለውጥ እንደማይኖር ተናግረዋል
ማንችስተር ዩናይትድ አዲሱ የእንግሊዝ ፕርሚየርሊግ ከመጀመሩ በፊት ተደጋጋሚ ጉዳቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
ቡድኑ እየደረጋቸው በሚገኙት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች አራት ወሳኝ ተጫዋቾቹን በጉዳት አጥቷል
ባሳለፍነው ቅዳሜ ከአርሰናል ጋር ባደረጉት የአቋም መለኪያ ግጥሚያ በ52 ሚሊየን ፓውንድ የተገዛው አዲሱ ተከላካይ ሌኒ ዮሮ ለሶስት ወራት ከሜዳ የሚርያቀው ጉዳት ሲያጋጥመው በተመሳሳይ አጥቂው ራስመስ ሆሉንድ 6 ሳምንታትን ለቡድኑ ግልጋሎት የማይሰጥበት ጉዳት ደርሶበታል፡፡
በዚህም አዲሱ የቡድኑ ተከላካይ ዮሮ ዩናይትድ በሊጉ ጅማሮ ከሊቨርፑል ፣ ቶተንሀም እና አስቶንቪላ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ አይሰለፍም፡፡
በተጨማሪም በቅዳሜው ጨዋታ በአርሰናል ላይ አንድ ግብ ያስቆጠረው ሆሉንድ መስከረም አንድ ከሊቨርፑል ጋር በኦልትራፎርድ በሚደረገው ጨዋታ እንደማይሰለፍ ታውቋል፡፡
ዩናይትድ በትላንትናው እለት በቅድመ ውድድር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች የላሊጋውን ቡድን ሪያል ቢትስን 3ለ2 ሲያሸንፍ ማርከስ ራሽፎርድ እና አንቶኒ ጉዳት ማስተናገዳቸው ታውቋል፡፡
ባለፈው የውድድር አመት በጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት 12 ጨዋታዎችን ብቻ ያደረገው የ22 አመቱ አይቮሪኮስታዊ የክንፍ ተጫዋች አማድ ዲያሎ በትላንቱ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
በጨዋታው በቀኝ ቁርጭምጭሚቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት ከሜዳ ከመውጣቱ በፊት የቡድኑ አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድ በፍጹም ቅጣት ምት አንድ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡
ሌላኛው በጨዋታው ጉዳት ያስተናገደው ብራዚላዊው አጥቂ አንቶኒ በ86ኛ ደቂቃ ላይ በጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ ይህን ተከትሎም ዩናይትድ በሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በአጠቃላይ 4 ተጫዋቾችን በጉዳት ማጣቱ ተረጋግጧል፡፡
ራሽፎርድ እና አንቶኒ ያጋጠማቸው ጉዳት እስከመች ከሜዳ እንደሚያርቃቸው በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም በፈረንጆቹ ነሀሴ 10 በኮሚኒቲ ሽልድ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ቡድኑ ለሚኖርበት ግጥሚያ የተጫዋቾቹ ጉዳት ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል ተብሏል፡፡
የእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ የቡድን ጥልቀት ላይ የሞት ሽረት ትግል ማድረግ እንደሚኖርበት የቡድኑ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የዘንድሮው የዝውውር መስኮት ከመጠናቀቁ በፊት የቡድኑን ስብስብ የሚያጠናከሩ ተጫዋቾችን ማስፈረም ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት ካልሰራ የውጤት ለውጥ አይኖርም ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም “ሁሉም ተጫዋቾች ከጉዳት ውጭ በጥሩ አቋም ላይ ሲሆኑ ጨዋታዎችን እናሸንፋለን ጉዳት በሚያጋጥመን ጊዜ ግን ተጨዋቹን ተክቶ ሊጫወት የሚችል ጥሩ አቅም ያለው ተጫዋች እጥረት ስላለብን እንሸነፋለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በጉዳት መደራረብ ምክንያት ተጨዋቾች ላይ የሚፈጠር ጫና ቡድኑ ውጤት እንዲርቀው ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
ዩናይትድ በአሜሪካ እያደረገ የሚገኝውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች በመጪው ቅዳሜ ከሊቨርፑል ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ያጠናቅቃል፡፡