የቦልሴናሮ ደጋፊዎች ሉላ ዳ ሲልቫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ የብራዚል ጦር ጣልቃ እንዲገባ ጠየቁ
የሀገሪቱ የምርጫ ባለስልጣን ባለፈው እሁድ ሉላ 51 በመቶ ያህል ድምጽ ማሸነፋቸውን አውጇል
ቦልሴናሮ ምንም እንኳን የስልጣን ሽግግሩ እንዲጀምር ትእዛዝ ቢያስተላልፉም፤ ውጤቱን ግን በይፋ አልተቀበሉም
የብራዚል ፕሬዚዳንት ጃይር ቦልሴናሮ ደጋፊዎች ረቡዕ እለት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ መመረጣቸውን ተከትሎ የጦር ሠራዊቱ ጣልቃ እንዲገባ በአደባባይ ሰልፍ ጠይቀዋል።
ደጋፊዎቹ በሳኦ ፓውሎ እና በሪዮ ዴ ጄኔሮ ትእይንተ ህዝብ አካሂደዋል። የብራዚልን ቢጫና አረንጓዴ ሰንደቅ አላማ በመያዝ ፀረ-ሉላ መፈክሮችን ማሰማታቸውን ሪዮተርስ ዘግቧል።
ሰልፈኞቹ ምርጫው መጭበርበሩን በመጥቀስ የሀገሪቱ ጦር ጣልቃ እንዲገባ ወትውተዋል።
ተመሳሳይ ድጋፎች የሀገሪቱ መዲና ብራዛቪሊያን ጨምሮ፤ ከ26 ግዛቶች በ24ቱ የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል ተብሏል።
የብራዚል መከላከያ ሚንስቴር ጣልቃ ይግባ ስለመባሉ ምላሽ ሲሰጥ፤ ሰላማዊ ሰልፍ በብራዚል ህግ መሰረት ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ አካል ነው ብሏል። ሚንስቴሩ አክሎም "ተቋሙ በፌደራል ህገ-መንግስት የሚመራ ነው" ብሏል።
የቀድሞ የጦር አዛዥ የሆኑት ቦልሴናሮ ከፈረንጆቹ 2018 ምርጫ ጀምሮ ከጦሩ ጋር ጠንካራ ትስስር በማዳበር ድጋፍ እንዳላቸውም ዘገባው አንስቷል።
አብዛኞቹ ወግ አጥባቂ ብራዚላውያን በፈረንጆቹ ከ1964 እስከ 1985 ለነበረው ወታደራዊ አገዛዝ እንዲመለስ ይሻሉም ተብሏል። በሌላ ጎን ደግሞ ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ በ1970ዎቹ ወታደራዊ መንግስትን በመቃወሞ ታስረዋል።
ተመራጩ ሉላ በጥር ወር የብራዚል ፕሬዝዳንትነት ስልጣን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።