ሮማሪዮ በብራዚን 2ኛ ዲቪዚዮን ላይ ለሚገኝ የእግር ኳስ ክለብ ነው የሚጫወተው
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሮማሪዮ በ58 ዓመቱ ወደ እግር ኳስ ጨዋታ ሊመለስ መሆኑን አስታወቀ።
ሮማሪዮ እግር ኳስን አቁሞ ታኬታ ከሰቀለ ከ15 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ እግር ኳስ ተመልሶ ለብራዚሉ አሜሪካ የእግር ኳስ ክለብ ለመጫወት መወሰኑን አስታውቋል።
ከሀገሩ ብራዚል ጋር የ1994 የዓለም ዋንጫ ያነሳው ሮማሪዮ በአሁኑ ወቅት በብራዚል ሊግ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ላይ ለሚገኘው አሜሪካ የእግር ኳስ ክለብ ለመጫወት በይፋ መመዝገቡን ባሳለፍነው ረቡዕ አስታውቋል።
"ለምወደው አሜሪካ የእግር ኳስ ክለብ በጥቂቱም ቢሆን የምችለውን ያክል ለማበርለት ዝግጁ ነኝ" ብሏል ሪማሪዮ በኢንስታግራም ገጽ ባወጣው መረጃ።
የ30 ዓመቱ የሮማሪዮ ልጅ ሮማሪንሆም ለብራዚሉ አሜሪካ የእግር ኳስ ክለብ በመጫወት ላይ ነው የሚገኘው።
ይህንን አስመልክቶም ሮማሪዮ በሰጠው አስተያየት፣ "ከልጄ ጋር በአንድ ሜዳ ላይ የመጫወት ህልሜ እውን የሚሆንበት ጊዜ ደርሷል" ብሏል።
"ከአሜሪካ እግር ኳስ ክለብ ጋር በሚኖረኝ ቆይታ የተወሰኑ ጨዋታዎችን ብቻ ተሰልፌ እጫወታለሁ" ያለው ሪማሪዮ፣ "ከልጄ ጋር የመጫወት ህልሜንም እውን አደርጋለሁ" ሲልም ተናግሯል።
ሮማሪዮ በአባቱ በጣም ተወዳጅ የነበረውን አሜሪካ እግር ኳስ ክለብ እየደገፈ ያደገ ቢሆንም፣ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ጨዋታውን የጀመረው በቫስኮ ዳጋም ክለብ ነው።
በዚያም ወደ አውሮፓ በማቅናት ለፒ.ኤስ.ቪ ኢንድሆቨን እና ለባርሴሎና ተሰልፎ መጫወት ችሏል።
በፈረንጆቹ 1994 በአሜሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ ከብራዘለል ጋር ተሰልፎ የዓለም ዋንጫን ያነሳ ሲሆን፣ በዚያው ዓመትም የፊፋ ኮከበ ተጫዋችነት ሽልማትንም አሸንፏል።
ብራዚላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሮማሪዮ በፈረንጆቹ 2008 ላይ ከእግር ኳስ ጨዋታ ራሱን በማግለል ታኬታ ሰቅሎ እንደነበር ይታወሳል።