የ”ቪንላደን” አባት ሁለተኛ ልጃቸውንም ሳዳም ሁሴን የሚል ስም አውጥተውለታል
በፔሩ የ22 አመቱ ወጣት ስሙ ከተሰማራበት ዘርፍ ይልቅ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል።
በ2017 ለደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ከ15 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ሲመረጥ አነጋጋሪ መሆን የጀመረው ተጫዋች “ኦሳማ ቪንላደን” ይባላል።
ለዩኒየን ኮሜርሲዮ የሚጫወተው “ቪንላደን” የአልቃይዳውን መስራች ስም መጋራቱ ጫና እንደሚያሳድርበት ቢጠበቅም እስካሁን ምንም ችግር አልገጠመኝም ይላል።
ታናሽ ወንድሙ “ሳዳም ሁሴን” እንደሚባል የሚገልጸው “ቪንላደን” አባቱ ሶስተኛ ልጃቸውን “ጆርጅ ቡሽ” ብለው ለመሰየም ቢያቅዱም ሴት በመሆኗ ሳይሳካ መቅረቱን ለስፔኑ ጋዜጣ ማርካ ተናግሯል።
“ኦሳማ ቢላደን የአሜሪካን ሁለት ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ሲያፈራርስ ስሙ በአለም መገናኛ ብዙሃን ናኝቶ ነበር፤ በጥቅምት 2002 ስለተወለድኩም አባቴ ስያሜውን አውጥቶልኛል” ም ነው ያለው።
“ቪንላደን” ከአልቃይዳው “ቢንላደን” በመጀመሪያዋ ፊደል (ቪ) የሚለያይ ቢመስልም በስፔንኛ “ቪ” ፊደል ስትነበብ እንደ “ቢ” ነው።
ወጣቱ ተጫዋች ስሙን ለመቀየር ፈልጎ እንደነበር ባይክድም ያልተለመደውንና ከሽብርተኛ ጋር የሚያያዘውን ስም በሂደት ግን እንደተቀበለው ነው የገለጸው።
“በፔሩ ሂትለር የተባለ ስም አለ፤ አለምን ባዳነው እየሱስ የሚጠሩም አሉ፤ ነገር ግን ጀሱስ ተብለው መጥፎ ነገር የሚሰሩ እንዳሉም ይታወቃል” የሚለው “ቪንላደን”፥ ስምና ምግባር ለየቅል መሆናቸውን ይናገራል።
የፔሩው ወጣት ተጫዋች በስም ዙሪያ አስገዳጅ ህግ መውጣት አለ ብሎ ግን አያምንም።
ለራሱ ልጅ “ሳንቲያጎ” የሚል ስም ለመስጠት ማሰቡንና አባቱ እሰይማለሁ ካለ ግን “ጆርጅ ቡሽ” ይለዋል የሚል ስጋት እንዳለውም ገልጿል።