የቡድን 20 ጉባኤ አስተናጋጅ ብራዚል ከሰሞኑ የሽብር ጥቃት ሙከራ በኋላ የድህንነት ጥበቃዋን አጠናክራለች
የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ በኢኮኖሚና ድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት አድርጎ በመጪው ሰኞ መካሄድ ይጀምራል
ቡድን 20 የአለምን 80 በመቶ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የሚያንቀሳቀሱ ሀገራት ስብስብ ነው
በየአመቱ የአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሀገራትን የሚያሰባስበው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ በመጪው ሰኞ መካሄድ ይጀምራል፡፡
የአዘጋጇ ሀገር ብራዚል ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ የዘንድሮው ጉባኤ ርሀብ እና ድህነትን በመዋጋት፣ ኢኮኖሚ፣ ሴቶችን ማብቃት፣ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች እና ቀጠናዊ ውጥረቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚመክር ተናግረዋል፡፡
እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የአለም ንግድ ድርጅት ያሉ የአለምአቀፍ ተቋማትን አስተዳደር ማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን መዋጋት እና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማጠናከር በዘንድሮው ጉባኤ የሚመከርባቸው ተጨማሪ አጅንዳዎች ናቸው፡፡
የቡድኑ አባል ሀገራት በአመት 500 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሸቀጥ ወደ ሀገራቸው የሚያስገቡ ሲሆን ቻይና እና አሜሪካ ከአባል ሀገራቱ መካከል ከፍተኛውን ምርት በማስገባት እና በመላክ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡
በተጨማሪም የአለም 75 በመቶ ንግድ፣ 80 በመቶ የአለም አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እንዲሁም የምድር 60 በመቶ ህዝብ በእነዚህ ሀገራት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
ስብስቡ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ አምራች ሀገራትን በውስጡ ቢይዝም የተረጋጋ አለም አቀፍ ገበያ እና ፍትሀዊ የንግድ ስርአትን መዘርጋት ላይ ወደኋላ ቀርቷል በሚል ይተቻል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጦርነት እና በድህነት ወደኋላ የቀሩ ሀገራትን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለመደግፍ አላማ እንዳለው ቢናገርም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እነዚህ ቃልኪዳኖች እንዳልተፈጸሙላቸው በማንሳት እንደሚወቅሱት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተለይ ከብድር ማራዘም እና እፎይታ ጋር በተገናኘ የአፍሪካ፣ የእስያ እና የላቲን አሜሪካ ሀገራት ቡድኑ አሰራሩን እንዲያሻሻል ተደጋጋሚ ጥያቄን ያቀርባሉ፡፡
ከነገ በስቲያ ሰኞ በሪዮ ዲጂኔሮ የሚካሄደው ጉባኤ ከሰሞኑ በብራዚል የተከሰተውን የሽብር ጥቃት ሙከራ ተከትሎ የደህንነት ስጋት አጥልቶበታል፡፡
በዚህ የተነሳም የመሪዎችን ደህንነትን ለማረጋገጥ ብራዚል ወታደሮችን፣ የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን እና የባህር ኃይል መርከቦችን አሰማርታለች።
ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) መጠቀም የተከለከለ ሲሆን ጉባኤው በሚካሄድበት አቅራቢያ በሚገኘው ሳንቶስ ዱሞንት አውሮፕላን ማረፊያ ለሁለት ቀናት በረራዎች ተሰርዘዋል።
ከዚህ ባለፈም 2900 ወታደሮችን ጨምሮ 26 ሺህ የጸጥታ አባላት ጉባኤው በሚካሄድበት አዳራሽ እና በአቅራቢያው በሚገኙ ስፍራዎች እንደሚሰማሩ ተሰምቷል፡፡
በጉባዔው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የቻይናው ሺ ጂንፒንግ እና የህንዱን ናሪንድራ ሞዲን ጨምሮ የ84 ሀገራት መሪዎችና ሚኒስትሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡