ቶማስ ቱኸል የቀድሞውን እንግሊዛዊ ስመ ጥር ተጫዋች ሊተኩ እንደሚችሉ ተገምቷል
ቼልሲ ከባድ ነበር ባለው ውሳኔ ከክለቡ ዋና አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድ ጋር ለመለያየት መወሰኑን አስታወቀ፡፡
ስንብቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የቀድሞ ዝነኛ ተጫዋቹን ያመሰገነው ክለቡ ከቅርብ የውድድር ጊዜያት ወዲህ እያስመዘገባቸው በመጡ ዝቅተኛ ውጤቶች ምክንያት ላምፓርድን ለማሰናበት መገደዱን አስታውቋል፡፡
በዘላቂነት ሊሻሻል እንደሚችል በውል ሊታወቅ ባልቻለበት ሁኔታ ክለቡ ከሊጉ አጋማሽ ላይ ተቀምጧል ሲልም ነው መግለጫው የሚያትተው፡፡
ከብዙ ማውጣትና ማውረድ በኋላ ከክለቡ ጋር የተጋመደ ደማቅ ታሪክ ያለውን አሰልጣኝ ለማሰናበት መወሰኑንም ገልጿል፡፡
ራሽያዊው የክለቡ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች ከአሰልጣኙ ጋር ባላቸው የቀረበ ግንኙነት፣ክብር እና ከታታሪነቱ አንጻር ምን ያህል ለውሳኔው ተቸግረው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡
በክለቡ የሚኖረው ክብር መቼም ቢሆን እንደማይቀንስ እና በማንኛውም ሰዓት ሊመለስ ቢችል ያለ አንዳች ማቅማማት ሊቀበሉት እንደሚችሉም አመስግነው መልካሙን ሁሉ እንዲገጥመው በተመኙበት ንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡
ላምፓርድ በአብራሞቪች የባለቤትነት ዘመን የተሰናበተ 10ኛው አሰልጣኝ ነው፡፡
ያለፉትን 18 ወራት በአሰልጣኝነት በስታምፎርድ ብሪጅ ያሳለፈው ላምፓርድ በባለፈው የውድድር ዓመት በፕሪሚዬር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ እስከ አራት ባለው ቦታ በመካተት ዓመቱን ለማጠናቀቅ ችሎ ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን በዚህ አቋሙ ሊቀጥል ክለቡን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማስጠጋትም አልቻለም፡፡ ያስፈረማቸው ቲሞ ዋርነርን መሰል ተጫዋቾችም ከሊጉ ቶሎ ተላምደው ለሚፈልገው ውጤት ሳያበቁት ቀርተዋል፡፡ ከባለፉት 8 የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችም በ5ቱ ተሸንፏል፡፡
ይህም ቼልሲ በሰንጠረዡ አጋማሽ 9ኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
ተሰናባቹ ጀርመናዊው የፒኤስጂ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል የቀድሞውን እንግሊዛዊ ስመ ጥር ሊተኩ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡