የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችን በተከታታይ የተመለከተው ቻይናዊ ፊቱ ፓራላይዝ ሆኗል
የሁዋን ከተማ ነዋሪው ቻኦ ለሰባት ቀናት ኳስ ሲመለከት ለሁለት ስአታት ብቻ ይተኛ ነበር
በገጠመው የጤና እክል ሆስፒታል የገባው የ26 አመት ኳስ አፍቃሪ በአጭር ጊዜ ሊያገግም እንደሚችል ሃኪሞች ተናግረዋል
በየአራት አመት የሚካሄደው የአለም ዋንጫ በበርካቶች ዘንድ ይጠበቃል።
ተጠባቂዎቹን ጨዋታዎች ለመመልከት ግን የአስተናጋጅ ሀገሪቱ የስአት አቆጣጠር ፈተና ሲሆን ይታያል።
ምንም ይሁን ምን አንድም የአለም ዋንጫ ጨዋታ እንዲያልፋቸው የማይፈልጉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ግን በአራቱም ማዕዘናት ይገኛሉ።
የሀገራቸው ብሄራዊ ቡድንም ባይሆን የእንቅልፍ ስአታቸውን ሰውተው ጨዋታዎችን በተከታታይ የሚመለከቱ የኳስ ወዳጆች ጥቂት አይደሉም።
ቻይናዊው ቻኦም ከነዚህ መካከል ይመደባል።
የ26 አመቱ የውሃን ከተማ ነዋሪ ለሰባት ቀናት በተከታታይ በሌሊት እንቅልፉን ሰውቶ ጨዋታዎችን ተመልክቷል።
ቻኦ ምንም እንኳን ሀገሩ ቻይና በአለም ዋንጫው ተሳታፊ ባትሆንም የኳታር የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች እንዲያልፉት አይፈልግም።
ከስራ እንደተመለሰ ብዙ ጊዜ ምሽት እና ሌሊት ላይ የሚደረጉትን ጨዋታዎች መመልከቱንም ተያይዞታል።
በየእለቱ የሚደረጉትን የምድብ ጨዋታዎችም ለሰባት ተከታታይ ቀናት በመመልከት አምሮቱን ለማውጣት ሞክሯል።
ቻኦ ጨዋታዎቹን ተመልክቶ አንድ ወይ ሁለት ስአት ተኝቶ ወደ ስራ መግባቱንም ቀጠለ።
ቻይናዊው የእግር ኳስ ወዳጅ “ቢሮ ሄጄ የተወሰነ አርፋለሁ” እያለ ለሰባት ቀናት ያጣው እረፍት ግን 8ኛው ቀን ላይ ዋጋ አስከፈለው።
“ለሁለት ስአት ብቻ ነበር የተኛሁት፤ ስነቃ ድካም ይሰማኝ ጀመር፤ ወደ ስራ ቦታ ስሄድም እየባሰብኝ መጣ፤ በድንገትም ከንፈሮቼ ወደ አንድ ጎን መጣመማቸውንና የአይኖቼ ቅንድቦች አልታዘዝ ማለት ጀመሩ” ይላል ቻኦ።
ጊዜያዊ ነገር ይሆናል ያለው ወጣት አልደነገጠም፤ ጤናውም በፍጥነት እንደሚመለስ አምኗል።
ነገር ግን እየባሰበት ሄዶ ሆስፒታል ለመግባት ተገደደ።
የሁዋን ከተማ ዶክተሮችም ቻኦ ፊቱ ፓራላይዝ መሆኑን አረዱት፤ ይሁን እንጂ ልዩ ህክምና ከተከታተለ ወደ ቀደመ ጤናው እንደሚመለስ ነገሩት።
የተጠራቀመ የእንቅልፍ እጦት እና በጣም ቀዝቃዛ በሆነ የአየር ጠባይ ጨዋታዎቹን መመልከቱ ለፊቱ ጡንቻዎች አለመታዘዝ ምክንያቶች መሆናቸውን በማንሳትም በቀናት ውስጥ ጤናው ሊስተካከል እንደሚችል ተናግረዋል።
የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ከቻኦ ሊማሩ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።