ከ3 አመቱ ጀምሮ እግር ኳስን ያፈቀረው ኪሊያን ምባፔ የልጅነት ህልሙን አሳክቷል
በትምህርት ቤት 2 ፓውንድ የማያወጣ “የአለም ዋንጫ”ን ለማንሳት ከጓደኞቹ ጋር የተጫወተው ምባፔ ዛሬ ሀገሩን ፈረንሳይ ወክሎ የአለም ውዱን ዋንጫ ለመሳም ይፋለማል
ህልሙን የኖረው የ23 አመቱ ኮከብ የልጅነት ትዝታውን ሲያወሳ አሰደናቂ ጉዞውን ይተርካል
የኪሊያን ምባፔ የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለ ከጓደኞቹ ጋር ያደረገው ትንቅንቅ ነው።
ለአሸናፊው ቡድን የተዘጋጀው ዋንጫም 1 ነጥብ 75 ፓውንድ የሚያወጣ የፕላስቲክ ዋንጫ መሆኑን ፈረንሳዊው ኮከብ ያወሳል።
በፓሪስ ቦንዲ በተባለች መንደር ያደገው ኪሊያን ምባፔ ከ3 አመቱ ጀምሮ ነው የእግር ኳስ ፍቅር ያደረበት።
ፔሌን እጅግ የሚወደው የያኔው ህጻን የመኝታ ክፍሉን በዜነዲን ዚዳን፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ኔይማር እና ሌሎች ኮከቦች ምስል አሸብርቆም ቀንም ሌትም ስለኳስ ማሰብ ይዟል።
“በሶስት አመቴ ፔዳል ያላት ባለአራት ጎማ መኪና ተገዝቶልኝ ነበር፤ እየነዳዋት ወደ ሜዳ እሄድ ነበር፤ በመጫዎቻዬ ጓደኞቼ ቢቀኑም እኔ ግን ቦታ አልሰጣትም ፤ ልቤ ከኳስ ጋር የተወዳጀ ነበር” ይላል ምባፔ።
ይህ የኳስ ወዳጅነቱ እያደገ ሄዶም የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለ የመጀመሪያውን “የአለም ዋንጫ” ፍልሚያ ማድረጋቸውንም ያወሳል።
“የ6ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች እያለን የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ጋር የ1 ነጥብ 75 ፓውንድ ዋንጫን ለማንሳት የሞት ሽረት ትግል አድርገናል” የሚለው ምባፔ፥
እያንዳንዱ ቡድን ሴቶችን ማካተት ግዴታው ስለነበር ሴቶችን የማሳመኑ ስራ ፈትኖት እንደነበር ያስታውሳል።
“የሴት ጓደኛዬን ከኛ ጋር ተሰልፋ ከተጫወተችና የምትችለውን ሁሉ ካደረገች ባለቀለም ደብተር እገዛልሻለሁ ብያታለሁ፤ እያጋነንኩ አይደለም ለፉክክሩ የሰጠነውን ቦታ ነው የሚያሳየው” ሲልም ይናገራል።
የ1 ነጥብ 75 ፓውንዱ የፕላስቲክ ዋንጫም እንደ ጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ትልቅ ቦታ እንደሰጡትም ነው ኪሊያን ምባፔ ከትሪቡን ጋር ባደረገው ቆይታ ያወሳው።
ምባፔ ኳስን ሲያሳድድ የቀለም ትምህርቱን እንደዘነጋውና ለመምህራኖቹም አስቸጋሪ ልጅ እንደነበር አልሸሸገም።
“አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስመለስ 9 ማስጠንቀቂያዎች የተጻፈበት ድብዳቤ ለቤተሰቦቼ እንዳደርስ ተሰጥቶኝ ነበር፤ ኪሊያን የቤት ስራ አልሰራም፣ የትምህርት መርጃዎቹን አልያዘም፣ በሂሳብ ክፍለጊዜ የሚያወራው ስለስፖርት ነው የሚሉት ይገኙበታል” ይላል ምባፔ።
አጥብቆ የተከተለው የኳስ ፍቅሩ ግን ዋጋውን አልነፈገችውም።
ፒ ኤስ ጂ ከሞናኮ ክብረወሰን በሆነ 162 ሚሊየን ፓውንድ ሲያዘዋውረው አለም በአግራሞት ተመለከተው እንጂ ያለፈበትን ጉዞ ብዙም አላወቀም።
በፈረንሳይ ሊግ አምስት ዋንጫዎችን አንስቷል፤ በ2018ትም ከፈረንሳይ ጋር የአለም ዋንጫን ከፍ አድርጎ የልጅነት ህልሙን እውን አድርጓል።
በፈረንሳይ ሶስት ጊዜ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብርን የተቀዳጀው የ23 አመት ወጣት ተጭዋች በኳታርም ነግሷል።
አምስት ጎሎችን አስቆጥሮ የወርቅ ጫማውን ለመውሰድ ከሊዮኔል ሜሲ ጋር እየተፎካከረ ነው።
ዛሬ በሉሳይል ስታዲየምም የፕላስቲክ ዋንጫውን ሳይሆን ከወርቅ የተዘጋጀውን ዋንጫ ከፍ አድሮ ለመሳም ይጫወታል።
ህልም አይከፈልበትምና ትልቅ ማሰብ ጥሩ ነው ግን ደግሞ በስራ ሊታገዝ ይገባዋል ይላል ህልሙን የኖረው ኪሊያን ምባፔ።