አለምአቀፉ ፍ/ቤት ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በተመለከተ ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ውሳኔ አሳለፈ
ደቡብ አፍሪካ፣ የእስራኤል ራፋን የመውረር እቅድ ተጨማሪ አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልገው እንደሆነ እንዲመረምረው ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ነው
አይሲጄ ፍልስጤማውያንን ለመጠበቅ ተጨማሪ አስቸኳይ እርምጃ አያስፈልግም የሚል ውሳኔ አሳልፏል
አለምአቀፉ ፍ/ቤት ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በተመለከተ ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ውሳኔ አሳለፈ።
አለምአቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት(አይሲጄ) ፍልስጤማውያንን ለመጠበቅ ተጨማሪ አስቸኳይ እርምጃ አያስፈልግም የሚል ውሳኔ አሳልፏል።
አይሲጄ የእስራኤልን የራፋ ጥቃት ተከትሎ የፍልስጤማውያን መብት ለማስጠበቅ ተጨማሪ አስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አስፈላጊቱ እንዳልታየው በትናንትናው እለት ገልጿል።
ፍርድ ቤቱ በጋዛ ሰርጥ እና በራፋ ያለው "አደገኛ ሁኔታ" በፈረንጆቹ ጥር 6፣2024 የተላለፉትን "ጊዜያዊ ውሳኔዎችን በአስቸኳይ እና ሙሉ በመሉ" በትዕዛዙ መሰረት መተግበር እንደሚፈልግ እና ተጨማሪ እርምጃ እንደማያስፈልግ ግልጽ አድርጓል።
ፍርድ ቤቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው እስራኤልን በዘር ማጥፋት የከሰሰችው ደቡብ አፍሪካ፣ የእስራኤል ራፋን የመውረር እቅድ ተጨማሪ አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልገው እንደሆነ እንዲመረምረው ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ነው።
ደቡብ አፍሪካ በእሰራኤል ላይ ያቀረበችውን ክስ የተመለከተው አይሲጄ፣ እስራኤል ጦሯ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይፈጽም እንድታደርግ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
ጋዛን ሲያስተዳድር ከነበረው ሀማስ ጋረ እየተዋጋች ያለችው እስራኤል ግን የቀረበባትን የዘር ማጥፋት ክስ አልተቀበለችውም።
እስራኤል በተለያዩ የጋዛ አካባቢዎች የተደረጉ ጦርነቶችን የሸሹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚገኙባትን በግብጽ ድንበር የምትገኘውን ራፋን ለማጥቃት እቅድ አውጥታለች።
ደቡብ አፍሪካ የእስራኤል ራፋን የማጥቃት እቅድ ፍርድ ቤቱ "ይህ የዘር ማጥፋት ህግን እና ፍርድ ቤቱ ጥር 26 ያስተላለፈውን ውስኔ የሚጥስ ነው" በሚል ነበር ተጨማሪ እርምጃ ያስፈልግ እንደሆነ እንዲመረመር ነበር የጠየቀችው።
ፍርድ ቤቱ ግን የባለፈው ውስኔ ተፈጻሚ ከሆነ በቂ ነው ሲል ወስኗል።
የእስራኤን ራፋን የማጥቃት እቅድ የግጭቱ አደራዳሪዎች እና ግብጽ ተቃውመውታል።
በተለይም ግብጽ እስራኤል በራፋ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ ከእስራኤል ጋር ከ40 አመታት በፊት በካምፕ ዴቪድ የፈረመችውን የሰላም ስምምነት ልትሰርዘው እንደምትችል አስፈራርታለች።