የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ እርዳታ እንዲገባ የሚያስችለውን የውሳኔ ሀሳብ አጸደቀ
የውሳኔ ሀሳቡን 13 ሀገራት ያጸደቁት ሲሆን ሩሲያ እና አሜሪካ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል
ተመድ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የሚደረገውን ድምጽ የመስጠት ሂደት ባለፈው ሳምንት ለበርካታ ጊዜ አራዝሞት ነበር
የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ እርዳታ እንዲገባ የሚያስችለውን ሀሳብ አጸደቀ።
የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ባልተጠበቀ ሁኔታ በጋዛ እርዳታ እንዲገባ የሚጠይቀውን በአረብ ኢምሬትስ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቆታል።
የውሳኔ ሀሳቡን 13 ሀገራት ያጸደቁት ሲሆን ሩሲያ እና አሜሪካ ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል።
አሜሪካ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ድምጸ ተአቅቦ ብታደርግም፣ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ የአረብ ኢምሬትስን ጥረት አመስግነዋል።
በአረብ ኢምሬትስ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ለጋዛ የሚደረገውን እርዳታ መጠን እንደሚጨምረው የገለጹት የአሜሪካ አምባሳደር እርዳታው ለተቸገሩት መድረስ አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
አምባሳደሯ አሜሪካ ወደ ጋዛ የሚገባው እርዳት እንዲጨምር ትሰራለች ብለዋል።
አምባሳደሯ ሀማስ ለዘላቂ ሰላም አይጨነቅም፤ በጥቅምት ወር የፈጸመውን አይነት ጥቃት ለመድገም ይፈልጋል የሚል ክስ አቅርበዋል።
ተመድ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ የሚደረገውን ድምጽ የመስጠት ሂደት ባለፈው ሳምንት ለበርካታ ጊዜ አራዝሞት ነበር።
በዛሬው እለት ሩሲያ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ያቀረበችውን ማሻሻያ አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን በመጠቀሟ ወይም ቬቶ በማድረጓ ምክርቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
እንግሊዝም በጋዛ እርዳት እንዲገባ ያስችላል የተባለውን የውሳኔ ሀሳብ ያቀረበችውን አረብ ኢምሬትስን አመስግናለች።
የውሳኔ ሀሳቡ እርዳታ እንዲገባ እንጅ ግጭት እንዲቆም የሚያደርግ ግን አይደለም።
ሩሲያ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ግጭት እንዲቆም የሚያስገድድ አንቀጽ እንዲገባ ያቀረበችው ሀሳብ በአሜሪካ ተቃውሞ አልጸደቀም።