በካንሰር ምክንያት ህይወታቸውን ከሚያጡ ሰዎች አንድ ሶስተኛው ሴቶች መሆናቸው ተገለጸ
ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት በካንሰር ምክንያት በርካታ ሴቶች እየሞቱ ነው
ከሳሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ያለው የካንሰር ስርጭት በሴቶች ላይ መበርታቱን አለም አቀፍ የሴቶች ጤና ህብረት አመላክቷል
ከሳሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ያለው የካንሰር ስርጭት በሴቶች ላይ መበርታቱን አለም አቀፍ የሴቶች ጤና ህብረት አመላክቷል፡፡
በአህጉሪቷ የጡት እና የማህጸን ጫፍ ካንሰር ስርጭት እያደገ እንደሚገኝ የህብረቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
በአፍሪካ ከ60-70 በመቶ ያሉ ሴቶች ካንሰሩ በሰውነታቸው ውስጥ ከተሰራጨ በኋላ ምርመራ የሚያደርጉ ሲሆን ከሁለት ሴቶች መካከል አንዷ ደግሞ በጡት ካንሰር እንደምትያዝ ነው የተነገረው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የጡት እና የማህጸን ካንሰር ከፍተኛ ስርጭት ካለባቸው 20 ሀገራት ከሳሀራ በታች ያለው ቀጠና 19ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
በኬንያ በአመት 7243 ሴቶች በጡት ካንሰር ሲያዙ 3398 ከካንሰር ጋር የተያያዙ ሞቶች ይመዘገባሉ፡፡
በአፍሪካ ሴቶች ቤተሰባቸውን እንዲሁም ሀገራቸውን በሚደግፍ ኢኮኖሚ ላይ እያደረጉት ያለው ተሳትፎ ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ መሄዱን ተከትሎ ለካንሰር ህክምና እና ክትትል በነፍስ ወከፍ አንድ ዶላር መመደብ ቢቻል የሴቶችን ጤና በመጠበቅ ኢኮኖሚው 3 ዶላር እንዲያመነጩ ማድረግ ይቻላል ተብሏል ፡፡
በአህጉሪቷ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እና የጤና መሰረተ ልማቶች አቅም መዳከም በግዜ መታከም ቢችሉ የሚድኑ የካንሰር በሽታዎች በሴቶች ላይ ክንዳቸውን ማበርታታቸው ተገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተያዘው አመት ጥር ወር ላይ የአለም ጤና ድርጅት እና አለም አቀፍ የሴቶች ጤና ህብረት ከአለም ኢኮኖሚ ፎረም ጋር ካንሰርን መከላከል አላማው ያደረገ ጥምረት ፈጥረዋል፡፡
ጥምረቱ በተለይ በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰቱ የካንሰር በሽታዎችን ለመከላከል የገቢ ማሰባሰብ፣ የጤና ተቋማትን ማጠናከር፣ የገንዛቤ ፈጠራን ማከናወን ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡
በአፍሪካ ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ካላቸው ሰፊ ሀላፊነት የተነሳ የግል ጤናቸውን መከታተተል እና መጠበቅ ላይ ደካማ ናቸው ያለው ጥምረቱ ይህን ለመቀየር መንግስታት በፖሊሲ ደረጃ ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያሳሰበው፡፡
በ2022 በአለም አቀፍ ደረጃ የማህጸን እና ጡት ካንሰር ከካንሰር በሽታዎች በስርጭት መጠናቸው 4ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በዚሁ አመት 660ሺህ አዲስ ታማሚዎች ሲመዘገቡ 350 ሺህ ሞት አልያም 94 በመቶው ሞት የተከሰተው በደሀ እና መካከለኛ ገቢ ባለባቸው ሀገራት ነው።