የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በደቡብ ኮሪያ ገቡ
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በሴዑል የሁለት ቀናት ጉብኝት ደርጋሉ
ፕሬዝዳንቱ ይፋዊ ጉብኝቱን የሚያደርጉት በደቡብ ኮሪያ አቻቸው ዮን ሱክ የል በተደረገላቸው ግብዣ ነው
የአረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በደቡብ ኮሪያ የመጀመሪያ ይፋዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ በዛሬው እለት ሴኡ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በቀድሞ ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገጻቸው ላይ በዛሬው እለት ሴዑል ደርሻለሁ፤ ከደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጋር ቆይታ ይኖረኛል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ለይፋዊ ጉብኝቱ ወደ ሴዑል ያቀኑት በደቡብ ኮሪያ አቻቸው ዮን ሱክ የል በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት ነው።
በሴኡል የሁለት ቆይታ የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሀመድ ቢን ዛይድ በንግድ፣ ኢንቭስትመንት፣ ኢነርጂ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የሀገራቱን ትብብር የሚያሳድጉ ምክክሮችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ጋር በሚኖራቸው ቆይታ ከሁለትዮሽ ባሻገር በቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ምክክር ያደርጋሉ።
ኤምሬትስ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ልዩ ስትራቴጂካዊ ትብብር በመመስረት ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ቀዳሚዋ ናት።
የአረብ ኢምሬትስና የደቡብ ኮሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ የጀመረው በፈረንጆቹ 1980 ሲሆን፤ ይህም ደቡብ ኮሪያ በአቡዳቢ ኤምባሲዋን ስትከፍት ነው።
አረብ ኢምሬትስ ደግሞ ከሰባት አመት በኋላ (1987) ኤምባሲዋን በሴኡል የከፈተች ሲሆን፥ በ2010 የወታደራዊ አታሼ ቢሮዋን ከፍታለች።
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በኒዩክሌር ልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ በሳይበር ደህንነት እና ምግብ ዋስትና በትብብር በመስራት ላይ ናቸው።
በደህንነት፣ በጤና ጥበቃ፣ ባህል እና በመንግስት አስተዳደር በጋራ የሚያከናውኗቸው ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የኤምሬትስ መንግስት ይገልጻል።
በቀጣዮቹ ጥቂት አመታት በደቡብ ኮሪያ 30 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ያቀደችው ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ የሁለት ቀናት የሴኡል ጉብኝትም የሀገራቱን ልዩ ስትራቴጂካዊ ትስስር እንደሚያጎለብት ይጠበቃል።