ኔታንያሁ የራፋው ጥቃት በአሳዛኝ ሁኔታ በስህተት የተፈጸሙ ነው አሉ
እስራኤል ራፋን ለማጥቃት የወሰነችው፣ የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ በራፋ እንደሚገኝ በመግለጽ ነበር
እስራኤል በራፋ በመጠለያ ድንኳን ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 45 ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በደቡባዊ ጋዛ በራፋ አካበቢ የተፈጸመው ጥቃት በርካታ ንጹሃን ላይ ጉዳት ያደረሰው በስህተት እንደነበር እና ምርመራ እንደሚደረግበት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በራፋ እስካሁን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ንጹሃንን አስወጥተናል፤ ምንም እንኳን ንጹሃንን ኢላማ ላለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ብናድረግም ሳይታሰብ አሳዛኝ ስህተት ተፈጥሯል" ብለዋል።
እስራኤል በራፋ በመጠለያ ድንኳን ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 45 ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል።ይህ ጥቃት በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ውግዘትን አስከትሎባታል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን በኤክስ ገጻቸው ‘’በራፋ ለንጹሀን መከለያ የሚሆን ምንም አይነት ስፍራ አልተረፈም፣ ይህ ሀላፊነት የጎደለው ጥቃት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል’’ ሲሉ ጥቃቱን አውግዘዋል።
ከፈረንሳይ ፕሬዝደንት በተጨማሪ የጀርመን፣ የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጥቃቱ ሊወገዝ የሚገባው እንደሆነ እና አለምአቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ያሳለፈው የተኩስ አቁም ወሳኔ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
እስራኤል በግብጽ ድንበር የምትገኘውን የራፋ ከተማ እንዳታጠቃ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ጫና አድርገው ነበር። ነገርግን እስራኤል ጫናውን ወደ ጎን በመተው ማጥቃቷን ቀጥላለች።
እስራኤል ራፋን ለማጥቃት የወሰነችው፣ የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ በራፋ እንደሚገኝ በመግለጽ ነበር።
ስምንት ወራትን ባስቆጠረው የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት፣ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ35ሺ ማለፉን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።