ግጭቶች ለጤና ቀውስ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል ተባለ
20 ሚልየን ህጻናት በአለም አቀፍ ደረጃ በክትባት እጥረት ምክንያት በበሽታ እየተሳቀዩ ነው
በአለም አቀፍ የጤና ጉዳዮች ዙርያ ይመክራል የተባለው የአለም ጤና ጉባኤ በፈረንጆቹ ሰኔ አንድ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራል
በተለያዩ የአለም ክፍሎች በመካሄድ ላይ የሚገኙ ግጭት እና ጦርነቶች በአለም አቀፍ ደረጃ የጤና ቀውስ እንዲባባስ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ተናግረዋል፡፡
ዋና ጸሀፊው የአለም ጤና ድርጅት ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው የአለም ጤና ጉባኤ በሚያደርገው አመታዊ ስብሰባ ለዚህ ችግር መፍተሄን እንዲያፈላልግ ጠይቀዋል፡፡
አዋና ጸሀፊው የአየር ንብረት ለውጥ፣ድህነት፣ በሰዎች መካከከል ያለው ሰፊ የኑሮ ልዩነት እና እየተበራከተ የሚገኘው ግጭት ለሰው ልጆች ስጋትን ደቅነዋል ብለዋል።
ግጭቶች፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ እና ቀደም ብለው ያሉ የጤና እክሎች እንዲባባሱ አዳዲስ በሽታዎችም እንዲጨምሩ አድርገዋል ያሉት ዋና ጸኃፊው በ2024 ብቻ በመላው አለም በደንጌ ፣በኮሌራ እና በሌሎችም በሽታዎች ተይዘው ክትባት የሚሹ 20 ሚልየን ህጻናት መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል።
በጋዛ እና ሱዳን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጥይት ብቻ ሳይሆን መታከም ባልቻሉ ጉዳቶች፣በምግብ እጥረት እና በሌሎችም በሽታዎች በአደጋ ውስጥ ይገኛሉ ያሉት ጉተሬዝ በጤና ተቋማት ላይ የሚደረሱ ጉዳቶች መጠን በሀላፊነት ዘመኔ አይቸው የማላውቀው ነው ብለዋል፡፡
ጉተሬዝ አክለውም የጤና ጉባኤው አለም በአሁኑ ወቅት አየተጋፈጠቻቸው ባሉ እና በቀጣይ ሊኖሩ በሚችሉ የጤና ስጋቶች እና መፍተሄዎች ላይ ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በየአመቱ የሚደረገው የአለም ጤና ጉባኤ በዘንድሮው አመት ‘’ሁሉም ለጤና፣ ጤና ለሁሉም’’ በሚል መሪ ሀሳብ ከመጭው ሰኔ አንድ ጀምሮ መከናወን ሲጀምር በጉባኤ ላይ 200 የሚደረሱ ሀገራት እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንድርሌይን ጉባኤውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት አለም በወቅታዊ የጤና ጉዳዮች ላይ መተባበር ካልቻለ ሁኔታዎች ሊባባሱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ከፍተኛ የጤና ቀውስ ባለባቸው ሀገራት የሚደረጉ ድጋፎች ካልተጠናከሩ በጦርነት ከሚሞተው ሰው እኩል በጤና ቀውስ ልናጣ እንችላለን ብለዋል።
በድጋፍ ደረጃ ህብረቱ ከአለም ጤና ድርጅት ጋር እየሰራ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ ባለፉት አምስት አመታት ከመቼውም ግዜ በበለጠ ከተለያዩ አካለት ገንዘብ በማሰባሰብ ለድርጅቱ ድጋፍ ማደረጉን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም በአፍሪካ ሀገራት የክትባት ማምረቻዎች እንዲቋቋሙ ድጋፍ መደረጉን ነው ያነሱት፡፡
የ77ኛው የአለምጤና ጉባኤ የቦትስዋናውን የጤና ሚንስትር ኤድዊን ዲኮሎቲን ፕሬዝዳንቱ አደርጎ መርጧል