የጋዛ ነዋሪዎች የቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ከፍርስራሽ ውስጥ እያወጡ በስርአት እየቀበሩ ነው
እስራኤል እና ሀማስ መካከለኛው ምስራቅን ያመሰቃቀለውንና ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቀም ስምምነት ላይ ደርሰዋል
ሀማስ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው መጠነሰፊ የእግረኛና የአየር ጥቃት ከ47 ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል
የጋዛ ነዋሪዎች የቤተሰቦቻቸውን አስከሬን ከፍርስራሽ ውስጥ እያወጡ በስርአት እየቀበሩ ነው።
እስራኤል እና ሀማስ መካከለኛው ምስራቅን ያመሰቃቀለውንና ለ15 ወራት የዘለቀውን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቀም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ይህን ተከትሎ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ በርካታ የጋዛ ነዋሪዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት ከፈራረሱ ህንጻዎች ውስጥ በመፈለግ ላይ ናቸው።
ሮይተርስ ሚስቱና አምስት ልጆቹ የጠፉበትና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኖ ያገኘውን አቡ ዳልፋን ማናገሩን ገልጿል። የአቡ ባለቤት እና አምስት ልጆቹ ከሌሎች 35 የቤተሰብ አባላት ጋር የተገደሉት እስራኤል በታህሳስ 2023 በጋዛ ከተማ ሸጃይኣ ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ነበር።
"ልጆቼ እስካሁን በፍርስራሽ ውስጥ ናቸው። ለማውጣት እየሞከርኩ ነው። የሲቪል ዲፌንስ ቡድን መጥቷል፤ ነገርግን ውድመቱ የማውጣት ስራውን ከባድ አድርጎባቸዋል። ሰማዕታትን ለማውጣት በቂ መሳሪያ ያለንም። ኤክስካቫተር እና ብዙ የቴክኒክ መሳሪያዎችን እንፈልጋለን"ብሏል አቡ።
በሙስሊም እና በአረብ ማህበረሰብ በአብዛኛው የሚቀበረው ከሞቱ ከሰአታት በኋላ ሲሆን ይህን ማድረግ አለመቻልና በክብር አለመቅበር ለሟች ቤተሰቦች እረፍት የሚነሳ ነው።
የፍልስጤም ሲቪል ዲፌንስ አገልግሎትና የጤና ባለሙያዎች በሀማስ እና እስራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ከባለፈው እሁድ ጀምሮ 200 አስከሬኖችን ከፍርስራሽ ውስጥ ማውጣታቸውን ገልጸዋል።
የጋዛ ጦርነት የተጀመረው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በደቡብ እስራኤል ጥቃት በመክፈት 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 250 ሰዎችን ደግሞ አግቶ ከወሰደ በኃላ ነው። ቢያንስ 94 ታጋቾች በጋዛ ውስጥ በህይወት እንዳሉ ይታመናል።
ሀማስ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው መጠነሰፊ የእግረኛና የአየር ጥቃት ከ47 ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
የሲቪል ዲፌንስ አገልግሎቱ ኃላፊ መሀሙድ ባሴል ቁፋሮው በከባድ ማሽነሪዎች እጥረት ምክንያት ችግር እንደገጠመው እና በጦርነቱ ከተገደሉት ውስጥ የ10ሺ ገደማ ፍልስጤማውያን አስከሬን አለመገኘቱንና አለመቀበሩን ተናግሯል።