ትራምፕ የጋዛው ተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂነት ላይ እምነት እንደሌላቸው ተናገሩ
ይህ የትራምፕ አስተያየት በእስራኤል ካቢኔ ጦርነቱ እንዲቀጥል ከሚፈልጉ ሚኒስትሮች ጫና ጋር ተዳምሮ የተኩስ አቁሙን ዘላቂነት አጠራጣሪ አድርጎታል
ከሰሞኑ በጋዛ የተለያዩ ስፍራዎች የተደራጀ ትጥቅ ታጥቀው የሚታዩ የሀማስ ታጣቂዎች መበራከት እስራኤል በጋዛ አሳክቸዋለሁ ያለችውን አላማ ጥያቄ ውስጥ ከቷል
ለጋዛው የተኩስ አቁም ስምምነት እውን መሆን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የገለጹት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስምምነቱ ዘላቂነት ላይ እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በጋዛው ጦርነት ዙሪያ የሰነዘሩት “ተስፋ አስቆራጭ” አስተያየት በስምምነቱ ዘላቂነት እና በአዲስ ጦርነት መጀመር ላይ ትልቅ እንድምታ ያለው ንግግር መሆኑን ተንታኞች ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ ከበዓለ ሲመቱ በኋላ ከጦርነቱ ተከትሎ ጋዛን የሚያስተዳድረው ማነው ተብለው ተጠይቀው፤ “ከዚህ ቀደም የነበሩት አካላት (ሀማስ) እንደማይሆኑ ተስፋ አድርጋለሁ ምክንያቱም ብዙዎቹ በጦርነቱ ሞተዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የስምምነቱን መዝለቅ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየትም “ስለ ስምምነቱ መቆየት እርግጠኛ አይደለሁም፤ ይህ የእኛ ጦርነት ሳይሆን የእነርሱ ጦርነት ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
ሲኤንኤን በዘገባው ይህ ሀሳብ “ስኬታችንን የምንለካው ባሸነፍናቸው ጦርነቶች ብቻ ሳይሆን ባቆምናቸው ጦርነቶችም ጭምር ነው” በሚል ትራምፕ ካደረጉት ቃልኪዳን መሰል ንግግር ጋር የሚጋጭ ነው ብሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን አስተያየት የሰነዘሩት የቀኝ ዘመም የእስራኤል ፖለቲከኞች የጦርነቱ መቆም ለሀማስ እንጂ ለእስራኤል አልጠቀመም በሚል ስምምነቱ እንዲቋረጥ እና ጦርነቱ ድጋሚ እንዲጀመር ግፊት እያደረጉ በሚገኙበት ጊዜ ነው፡፡
ከእስራኤል መንግስት አጣማሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው “ጂውሽ ፓወር ፓርቲ” መሪ እና የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ኢታማር ቤንጊቨር ስምምነቱን በመቃወም ከሃላፊነታቸው ለቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች የተኩስ አቁም ስምምነቱ የመጀመርያው የ 42 ቀናት ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነትን አቋርጠው ወደ ውጊያ ካልተመለሱ ከሀላፊነታቸው እንደሚለቁ ዝተዋል፡፡
ሚንስትሩ አክለውም "ሀማስን ለመደምሰስ እና ይህን ስጋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት እስራኤል ወደ ጦር ሜዳ እንደምትመለስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ቃል ገብተውልኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስምምነቱ ተግባራዊ በተደረገበት እሁድ ዕለት “እስራኤል በሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ሂደት ላይ የሚደረገው ድርድር ፍሬ አልባ ነው ብላ ካመነች ወደ ጦርነት የመመለስ መብት እንዳላት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ፕሬዝዳንት ባይደን ማረጋገጫ ሰጥተውናል ብለዋል፡፡
የካቲት አራት የሚጀምረው እና የእስራል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጡ የሚያዘው ሁለተኛው ምዕራፍ ገቢራዊ ከመሆኑ በፊት ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት እስከ እስራኤል ሚኒስትሮች እየተናፈሰ ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት ዘላቂነት ጥርጣሪ ለታጋች ቤተሰቦች ስጋት መፍጠሩን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታጋቾች በተለቀቁበት ወቅት እና በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት ቁፋሮ በሚከናወንባቸው ስፈራዎች በተደራጀ ሁኔታ የታጠቁ የሀማስ ታጣቂዎች በስፋት መታየታቸው በጋዛው ጦርነት እስራኤል አሳክቸዋለሁ ያለችው ሀማስን የማጥፋት አላማ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር “ሃማስን ማዳከም ብንችልም ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅሙን የማፍረስ ዓላማችንን አላሳካንም” ሲሉ አምነዋል።
የአሜሪካ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው እስራኤል በርካታ የሀማስ ታጣቂዎችን የመደምሰሷን ያህል ቡድኑ በዛው ልክ ብዙ አዳዲስ ታጣቂዎችን መመልመሉን ተናግረዋል፡፡
እነኚህ ሁሉ ሁኔታዎች ከትራምፕ አስተያየት እና በኔታንሁ መንግስት ላይ እየበረታ ከሚገኝው ጫና ጋር ሲታከሉ የ15 ወራቱ ጦርነት ሊቀጥል የሚችልበት እድል ሰፊ እንደሚሆን ተዘግቧል፡፡