የሳህል ቀጠና ወታደራዊ መንግስታት ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ በጋራ 5 ሺህ ጦር ሊያሰማሩ ነው
ፈረንሳይን ጨምሮ ከሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጋር ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ያቋራጡት ሀገራት በማዕከላዊ ሳህል የጋራ ጦር ለማሰማራት ተስማምተዋል
ሀገራቱ የመሰረቱት ወታደራዊ ጥምረት የራሱ የአየር ሀይል መሰረተ ልማቶች ፣ የጦር መሳሪ እና የደህንነት መረጃዎች እንደሚሟላለት ተነግሯል
በወታደራዊ መንግስት የሚመሩት የምዕራብ አፍሪካ ጎረቤታም ሀገራት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የጋራ ጦር ለማሰማራት ተስማምተዋል፡፡
ከኒጀር ፣ ቡርኪናፋሶ እና ማሊ የተውጣጡ 5 ሺህ ወታደሮችን ያቀፈ የጦር ሃይል በቅርቡ የጸጥታ ችግር በበዛበት ማዕከላዊ ሳህል ቀጠና እንደሚሰፍር የኒጀር የመከላከያ ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡
በአጎራባች ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በፈረንጆቹ 2020 እና 2023 መካከል በተደረጉ ተከታታይ መፈንቅለ መንግስቶች ወታደራዊ መሪዎች የመንግስት ስልጣንን ተቆጣጥረዋል፡፡
መንግስታቱ ባለፈው አመት ከአካባቢው አጋሮች፣ፈረንሳይ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጋር የቆየውን ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካቋረጡ በኋላ የጸጥታ ስጋቶችን በጋራ ለመፍታት ተስማምተዋል።
የኒጀር መከላከያ ሚንስትር ሳሊፉ ሞዲ አዲሱ ጦር “የሳህል ሀገራት ጥምረት” (ኤኢኤስ) በሚል ስያሜ በሶስቱ ሀገራት ግዛት ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ጦሩ የራሱ የአየር ሀይል መሰረተ ልማቶች ያሉት ፣ የጦር መሳሪያ የተደራጀ የስለላ እና መረጃ መረብ የተሟላለት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
አዲሱ ጥምረት ከሳምንታት በኋላ በተመረጡ ቦታዎች ላይ መሰማራት የሚጀመር ሲሆን ቀደም ብሎ በሶስቱ ሀገራት የጋራ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው ተብሏል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ከአልቃይዳ እና አይኤስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ጋር ለአስርተ ዓመታት በዘለቀው ውጊያ የተቀሰቀሰው ሁከት ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላም ተባብሶ ቀጥሏል።
በቀጠናው እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ 2.6 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተመድ የሰብአዊ ኤጀንሲ (ኦቻ) አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2020-2021 ብቻ የኢኮዋስ አባል ሀገራት ከሰላም እጦቱ ጋር በተያያዘ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 6.7 በመቶ ወይም 50 ቢሊየን ዶላር አጥተዋል፡፡
በአካባቢው ፈረንሳይ እና አሜሪካን ጨምሮ ሀገራት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ለአመታት ወታደሮቻቸውን አሰማርተው የቆዩ ቢሆንም የቀጠናው ደህንንት አሁንም በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ከ2020 ጀምሮ በአካባቢው በተካሄዱት በርካታ መፈንቅለ መንግስቶች ወታደራዊ አመራሮች ስልጣን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የምዕራባውያን ጦር ከሀገራቸው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡
የአሁኑ የሶስትዮሽ ህብረት መፈጠር ሀገራቱ ከምዕራባውያን ሀገራት እገዛ እና ከምዕራብ አፍሪካ ዋና የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቡድን (ኢኮዋስ) ለመውጣት መወሰናቸውን ተከትሎ ገቢራው የሆነ ነው ተብሏል፡፡