ሩስያ ፣ ቻይና ፣ ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ የሚፈጥሩት ጥምረት ለትራምፕ አስተዳደር ፈተና ሊሆን እንደሚችል ተነገረ
ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካን “ባላንጣዎች” ለማዳከም በሚያደርጉት ሙከራ የሀገራቱን ህብረት ማዳከም ላይ ሊሰሩ ይችላሉ ተብሏል
ከ2022 ወዲህ የአሜሪካ ዋና “ባላንጣዎች” ተብለው የሚጠሩት 4 ሀገራት ስትራቴጂካዊ አጋርነት እያደገ ይገኛል
ቻይና ፣ ኢራን ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ የሚፈጥሩት ጥምረት ለአዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ፈተና ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት የዋሽንግተን “ባላንጣዎች” ናቸው ተብለው በተለዩት ከሰሜን ኮሪያ እና ሩስያ ጋር ወዳጅነትን ለመፍጠር ሲሞክሩ በአንጻሩ በኢራን እና ቻይና ላይ ተጽዕኗቸውን አጠናክረው ታይተዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ሁኔታዎች ካለፈው ጊዜ የተለዩ ይመስላሉ። በ2022 ሩስያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" ተከትሎ እነኚህ የአሜሪካ ተቃዋሚዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተቀራርበዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት አመታት የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያልተገደበ አጋርነት ፈጥረዋል፡፡
ቤጂንግ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ከሞስኮ ጋር አጋር ሆና ቆማለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትላንትናው ዕለት ፑቲን እና ሺ ዢንፒንግ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ከፈፀሙ በኋላ በበይነ መረብ ባደረጉት ረጅም ውይይት ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሩሲያ በሰኔ 2024 ከሰሜን ኮሪያ ጋር ፣ ባሳለፍነው ሳምንት አርብ ደግሞ ከኢራን ጋር ስትራቴጂካዊ ስምምነቶችን ተፈራርማለች።
ባሳለፍነው ሰኞ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ የፈጸሙት ትራምፕ የኢራንን የኒዩክሌር መርሀ ግብር ለመግታት ፣ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እና የቻይናን መስፋፋት ለማስቆም ቃል ገብተዋል፡፡
በባይደን አስተዳደር በቻይና የአሜሪካ አምባሳደር “ያልተቀደሰ ጥምረት” ተብለው የጠሩት አራት የአሜሪካ “ጠላቶች” ስብስብ የዋሽንግተን እና አጋሮቿ አቅም እንዲዳከም እንደሚያደርግ ተንታኞች ይናገራሉ።
የትራምፕ አስተዳደር ከሩሲያ ጋር ለመስማማት ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻል። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ በቻይና ኢኮኖሚ ላይ ጫና ማሳደር ይፈልጋል፡፡
በዚህ ሂደት በቤጂንግ እና ሞስኮ መካከል ያለው አጋርነት በቻይና ላይ ማድረስ ያስበውን ተጽዕኖ እንዳያሳካ እንቅፋት እንደሚሆን በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የምስራቅ እስያ ፖሊሲን የመሩት ዳንኤል ሩሰል ይናገራሉ።
የቀጠናዊ ፖሊሲ ባለሙያው ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ውስጥ ለሩሲያ ወታደሮች እና የጦር መሳሪያዎች እያቀረበች ከመሆኗም በዘለለ የኒዩክሌር ሚሳይል ፕሮግራሟን በፍጥነት እያሳደግች እንደምትገኝ በተጨማሪ ገልጸዋል፡፡
ኢራን እስራኤል በቀጣናዊ አጋሮቿ ላይ ባደረሰችው ጥቃት በመካከለኛው ምስራቅ ያላት ተጽዕኖ ፈጣሪነት ቢዳከምም የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ለመገንባት ጥረቷን እንደገና ልትጀምር እንደምትችል ተንታኞች ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና ስታራቴጂያዊ አሰላለፍ ለውጦች በሚገኝበት ሁኔታ ትራምፕ ቃል እንደገቡት የአሜሪካን “ጠላቶች” ማዳከም ቀላል ላይሆን እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሀገራቱ መካከል እየተጠናከረ የመጣው ወዳጅነት የትራምፕ አስተዳደር ያሰበውን አይነት ውጤት እንዳያስመዘግብ እክል ሊሆን ስለሚችል ምናልባትም አጋርነቱን ለመበታተን ጥረት ሊያደርግ እንደሚችል ነው የተነገረው፡፡