በቻይና ሁቤይ ግዛት ዉሀን ከተማ የተከሰተው ኮሮና ቫይረስ በፍጥነት መስፋፋቱን ቀጥሏል፡፡
እስካሁን የኮሮና ቫይረስ ሟቾቹ ቁጥር 106 ሲደርስ የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው ደግሞ ትናንት ከነበረው 2,835 ዛሬ 4,535 ደርሷል፡፡ ቫይረሱ ህይወታቸውን የነጠቃቸው በሙሉ ቻይናውያን ናቸው፡፡
ቫይረሱ በአሁኑ ወቅት በመላው ቻይና መሰራጨቱ የተረጋገጠ ሲሆን ከቻይና ውጭ ደግሞ 17 ሀገራት ደርሷቸዋል፡፡
ከቻይና ውጭ ቫይረሱ በደረሰባቸው ሀገራት ከ60 በላይ ሰዎች መጠቃታቸው ነው የተዘገበው፡፡
ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ዉሀንን ጨምሮ ከ60 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርበት የሁቤይ ግዛት አሁንም እንደተዘጋ ነው፡፡ ወደ ግዛቱም ይሁን ከግዛቱ ወደ ሌላ አካባቢ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የለም፡፡
ይሁንና እገዳው ከመጣሉ በፊት 5 ሚሊዮን ያክል ህዝብ ከቻይ አዲስ ዓመት በዓል ጋር በተያያዘ ከዉሀን ከተማ እንደወTa የከተማዋ ከንቲባ ይፋ አድርገዋል፡፡
በአንዳንድ የቻይና ከተሞች አፍንጫና አፍን የሚሸፍን ጭምብል ማድረግ አስገዳጅ ሆኗል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ቻይና እየወሰደች ያለውን ጥረት ያደነቁት የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም ቻይና በሽታውን ሙሉ በሙሉ እንደምትቆጣጠር እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ ሀገራትም ከዉሀን ዜጎቻቸውን ለማስወጣቱ ሩጫ ላይ ናቸው፡፡ ጃፓን ወደ ከተማው አውሮፕላን የላከች ሲሆን አሜሪካም ዛሬ ዜጎቿን ለማስወጣት መሰል እርምጃ እንደምትወስድ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ በቻይና በተለይም በዉሀን ከተማ የሚኖሩ ዜጎቿ አስፈላጊዉን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ቤጂንግ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ክትትል እያደረገች መሆኑን ገልጻለች፡፡ በዉሃን ብቻ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እንዳሉ ነው መንግስት ያሳወቀው፡፡
ሆንግ ኮንግ ከእናት ሀገሯ ቻይና ጋር ከሚያገናኟት ወሰኖች የተወሰኑትን በጊዜያዊነት እንደምትዘጋ የከተማዋ ዋና ስራ አስፈጻሚ ካሬ ላም በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል፡፡
የቫይረሱ መነሻ በዉሀን ከተማ የሚገኝ የዱር እንስሳት እና የውሀ ዉስጥ እንስሳት ገበያ ሲሆን ቫይረሱ በእንስሳት ላይ የተለመደ ነው ተብሏል፡፡ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰውም ይተላለፋል፡፡
ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ የዱር እና የውሀ ዉስጥ እንስሳት ገበያው ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል፡፡
ሲኤንኤን፣ሲጂቲኤን እና ቢቢሲ የዘገባው የዘገባው ምንጮች ናቸው፡፡