ዝነኛው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኮቢ ብርያንት ከ13 ዓመት ልጁ እና ሌሎች 7 ሰዎች ጋር በሄሊኮፕተር አደጋ ሞተ፡፡
የ41 ዓመቱ ብርያንት፣ የ13 ዓመት ሴት ልጁ ጂያና እና ሌሎች 7 ሰዎች ታውዛንድ ኦክሰ ከተማ ወደሚገኘው ማምባ ስፖርት አካዳሚ በሚካሄድ የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ላይ ለመታደም በመጓዝ ላይ እያሉ በካሊፎርኒያ ካላባሳስ ከተማ አቅራቢያ ሄሊኮፕተሩ ተከስክሶ ህይወታቸው አልፏል።
የጉዟቸው አላማ የነበረው ጂያና በጨዋታው ልትሳተፍ አባቷ ኮቢ ደግሞ ጨዋታውን ለመምራት እና ለማሰልጠን ነው ተብሏል፡፡
ሄሊኮፕተሩ የተከሰከሰው በወቅቱ ከነበረው ከፍተኛ ጭጋጋማ አየር ጋር በተያያዘ እንደሆነ ነው የተዘገበው፡፡
የ41 ዓመቱ ጡረተኛ ተጫዋች ኮቢ የቅርጫት ኳስ ህይወቱን ለ20 ዓመታት በሌከርስ የቅርጫት ኳስ ቡድን በመጫወት ነው ያሳለፈው፡፡
ኮቢ በአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ (NBA) የ5 ጊዜ ሻምፒዮን ሲሆን ከምን ጊዜም ምርጥ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡
በርካታ የዓለማችን ዝነኞች፣ ፖለቲከኞች፣ ስፖርተኞች እና የስፖርቱ ዓለም አፍቃሪያን በኮቢ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን በተለያየ መልኩ እየገለጹ ነው፡፡
ምሽት በሎሳንጀለስ በተካሔደው የግራሚ አዋርድ ስነ-ስርዓት ላይም የኮቢ ማስታወሻ ዝግጅት ተካሂዷል፡፡
የሰሜን አሜሪካ ቅርጫት ኳስ ሊግ-ናሽናል ባስኬትቦል አሶሴሽን (NBA) ባወጣው መግለጫ፣ በኮቢ ብርያንት እና በልጁ ጂያና እጅግ አስደንጋጭና አሳዛኝ ሞት ክፉኛ ማዘኑን አስታውቋል፡፡ ኮቤ ለ20 ዓመታት በዘለቀው የቅርጫት ኳስ ህይወቱ የተለየ ተሰጥኦን ከማሸነፍ ፍላጎት ጋር በማጣመር ምን መፍጠር እንደሚቻል አሳይቶናል ሲልም ሊጉ ገልጿል፡፡
ሄሊኮፕተሩ ከሎሳንጀለስ ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ 30 ማይል ርቀት ላይ ኮረብታማ ስፍራ ላይ ነው የተከሰከሰው፡፡
በወቅቱ እሳት ተቀጣጥሎ እንደነበርም የሎሳንጀለስ እሳት አደጋ ዲፓርትመንት መረጃ ያሳያል፡፡
ምንጭ፡- ሲኤንኤን