በብሪክስ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ የዓለማችን ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል
ብሪክስ ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ ሀገራት በሙሉ ወደ ደቡብ አፍሪካው ጉባዔ መጋበዛቸው ተገለጸ
በብሪክስ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት ቁጥር መጨመሩ ተገለጸ።
በፈረንጆቹ 2009 ላይ በአምስት ሀገራት የተመሰረተው ብሪክስ የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
42በ መቶ የዓለማችን ኢኮኖሚ እና ህዝብ ብዛት ድርሻ ያለው ይህ ስብስብ በምዕራባዊያን የሚመራውን የዓለም ስርዓት በመገዳደር አማራጭ የመሆን ትልምን ይዞ መመስረቱ በተለያዩ ጊዜያት መገለጹ ይታወሳል።
ይህ ስብስብ ዓመታዊ የመሪዎች ጉባኤውን የፊታችን ነሀሴ 16 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ከተማ እንደሚያካሂድ ተገልጿል።
በዚህ ጉባኤ ላይ የበርካታ የዓለማችን ሀገራት በአካል እንደሚሳተፉ የጉባኤው አስተናጋጅ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ገልጻለች።
በተጨማሪም ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ የሁሉም ሀገራት መሪዎቸ ወደ ደቡብ አፍሪካ መጋበዛቸውንም ሀገሪቱ አስታውቃለች።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ የዓለማችን ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በዘንድሮው የብሪክስ ጉባኤ ላይ አባልነታቸው የሚረጋገጥላቸው ሀገራት ይኖራሉም ተብሏል።
ለአብነትም ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ካዛኪስታን እና ግብጽ ያቀረቡት የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚችል ይጠበቃል።
ፈረንሳይ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ጥያቄ ብታቀርብም ሩሲያ ፓሪስ በብሪክስ ጉባኤ ላይ እንድትሳተፍ ፍላጎት የለኝም ማለቷን ተከትሎ ያቀረበችው ጥያቄ ምላሽ አልተሰጠውም ተብሏል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ጉባኤ ላይ በአካል ይሳተፋሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ጋር በተያያዘ በተነሱ ጉዳዮች ምክንያት በአካል እንደማይገኙ መገለጹ ይታወሳል።