በብሪክስ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ጥያቄ ያቀረበችው ፈረንሳይ እስካሁን እንዳልተጋበዘች ተገለጸ
ሩሲያ ፈረንሳይ በብሪክስ እንድትጋበዝ አልፈልግም ማለቷ ይታወሳል
የብሪክስ ጉባኤ አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪካ ከፈረንሳይና አሜሪካ ውጪ 70 ሀገራትን ጋብዘዋል
በብሪክስ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ጥያቄ ያቀረበችው ፈረንሳይ እስካሁን እንዳልተጋበዘች ተገለጸ።
በፈረንጆቹ 2009 በአምስት ሀገራት የተመሰረተው ብሪክስ የፊታችን ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
የቡድን ሰባት አባል ሀገር የሆነችው ፈረንሳይ በዚህ ጉባኤ መካፈል እንደምትፈልግ በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል ይፋ አድርጋም ነበር።
ከብሪክስ መስራች ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሩሲያ ፈረንሳይ በብሪክስ ጉባኤ ላይ እንድትጋበዝ እንደማትፈልግ አስታውቃም ነበር።
የብሪክስ የወቅቱ ተሬዝዳንት የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ፈረንሳይን እንዳልሃበዘች ስፑትኒክ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ደቡብ አፍሪካ በብሪክስ ጉባኤ ላይ ከፈረንሳይ ውጪ 70 ሀገራትን ጋብዘዋል።
በብራዚል፣ ሕንድ፣ ሩሲያ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ህብረት የተመሰረተው እና በምህጻረ ቃሉ ብሪክስ በመባል የሚጠራው ስብስብ የምዕራባዊያንን ተጽዕኖ ለመመከት በሚል ነበር በፈረንጆቹ 2009 ላይ የተቋቋመው።
ዋና መቀመጫውን ቻይና ያደረገው ይህ የአምስት ሀገራት ስብስብ ከዓለም ህዝብ ብዛት ውስጥ 42 በመቶ ድርሻ አለው።
ብሪክስ በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ከሚመራው ቡድን ሰባት ሀገራት ስብስብ ጋር ሲነጻጸር በዓመታዊ ገቢም ሆነ በህዝብ ብዛት ይበልጣል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ30 በላይ የዓለማችን ሀገራት ብሪክስን በአባልነት ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል።
የነዳጅ ሀብታሟ ሀገር ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት የብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን ያቀረቡ ሲሆን ስብስቡ ለነዚህ ሀገራት ፈቃድ በቅርቡ እንደሚሰጥ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።