ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት የሚኒስትሮች ስብሰባ መካፈል ጀመረች
የብሪክስ አባል ሀገራት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሞስኮ ለሶስት ቀናት የሚያደርጉት ምክክር ተጀምሯል
ስብስቡን የተቀላቀሉት አምስት ሀገራት ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባው ልኡካቸውን እያሳተፉ ነው
የብሪክስ አባል ሀገራት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በሩሲያ መዲና ሞስኮ መካሄድ ጀምሯል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ2024 ብሪክስን የተቀላቀሉ አምስት ሀገራት እየተሳተፉ መሆኑን የኢራኑ የዜና ወኪል መኸር ኒውስ ዘግቧል።
ብሪክስ ባለፈው አመት ኢትዮጵያ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ ግብጽ፣ ኢራን እና ሳኡዲ አረቢያ ከጥር 2024 ጀምሮ ስብስቡን እንዲቀላቀሉ መወሰኑ ይታወሳል።
አምስቱ ሀገራት ለሶስት ቀናት በሞስኮ በሚካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ ከሩሲያ፣ ቻይና፣ ብራዚል፣ ህንድና ደቡብ አፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል።
የብሪክስ አባል ሀገራት በምዕራባውያን ኃያላን የሚመራውን ዓለም አቀፋዊ ስርዓትን ለመገዳደር መሰባሰብን መርጠው የንግድ ትብብራቸውም በየጊዜው እያሳደጉ ነው።
ሀገራቱ ቡድኑ ልማት፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ጥቅሞችን እንደሚከፍትም ተስፋ አላቸው።
የብሪክስ የ15 አመት ጉዞ
“ብሪክ” (BRIC) የሚለውን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው ብሪታኒያዊው የኢኮኖሚ ባለሙያ ጂም ኦኔይል ነው።
ከብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ቻይና ስያሜ የመጀመሪያ ፊደል ወስዶ “ብሪክ” የሚለውን ስያሜ ሲሰጥ በ21ኛው ክፍለዘመን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚያስመዘግቡ ሀገራት መሆናቸውን በመጥቀስ ነው።
የአራቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በፈረንጆቹ 2006 ሃምሌ ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ምክክር አድርገዋል።
“ብሪክ” የሚለው ስያሜ ጥቅም ላይ የዋለው ግን ሚኒስትሮቹ በመስከረም ወር 2006 ከመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በኒውዮርክ ምክክር ሲያደርጉ ነው።
የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤም በሰኔ ወር 2009 በሩሲያ አስተናጋጅነት መካሄዱ ይታወሳል።
“ብሪክ” ወደ “ብሪክስ” ያደገው ደቡብ አፍሪካ በ2010 በይፋ ቡድኑን ተቀላቅላ በ2011 የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ስትሳተፍ ነው።
የአለማችን 40 በመቶ ህዝብ እና ከ30 በመቶ በላይ ኢኮኖሚ የሚይዙ ሀገራት ስብስብ የሆነው ብሪክስ አሁን ላይ 10 አባላት ያሉት ቡድን ሆኗል።