ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ኤምሬትስ የብሪክስ አባል ሆና መመረጧን አደነቁ
ብሪክስ ለአለም እድገት በትብብር ለመስራት ትልቅ እድል ይፈጥራልም ነው ያሉት
የብሪክስ አባል ሀገራት አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ አዳዲስ አባል ሀገራት ብሪክስን እንዲቀላቀሉ ወስነዋል
አረብ ኤምሬትስ የብሪክስ አባል ሆና ተመርጣለች።
በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ እየተካሄደ ባለው የብሪክስ አባል ሀገራት ስብሰባ ነው አቡ ዳቢ የቡድኑ አባል እንድትሆን የተመረጠችው።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ባስተላለፉት የደስታ መልዕክት፥ የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ኤምሬትስ የቡድኑ አባል ለማድረግ ያሳለፉትን ውሳኔ አድንቀዋል።
“ወሳኝ” ነው ያሉት ቡድን ኤምሬትስን አባል ማድረጉ ለአለም ብልጽግና በጋራ ለመስራት ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና አርጀንቲናን የቡድኑ አዲስ አባል እንዲሆኑ ወስነዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቱ ብሪክስን መቀላቀል ብሪክስ በአለማቀፍ ደረጃ ተጽዕኖው ከፍ እንዲል እንደሚያደርግ ነው ያስታወቁት።
የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው፥ ውሳኔውን “ታሪካዊ ነው” ብለውታል።
ተጨማሪ ሀገራት ብሪክስን መቀላቀላቸው ለአለም ሰላም በጋራ ለመስራት ይበልጥ አቅም ይጨምራል ያሉት ደግሞ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ናቸው።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ደግሞ አዳዲሶቹ የብሪክስ አባል ሀገራት ብዝሃ ባህል ያላቸው መሆኑ የቡድኑን አካታችነት ያሳድጋል ነው ያሉት።
ኤምሬትስን ጨምሮ አዳዲሶቹ ብሪክስን እንዲቀላቀሉ የተመረጡት ሀገራት ከጥር 1 2024 ጀምሮ የቡድኑ አባል ይሆናሉ ተብሏል።
3ኛ ቀኑን የያዘውን የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ በቀጥታ ለመመልከት ሊንኩን ይጫኑ