የብሪክስ 10 አባል ሀገራት ከአለማችን ህዝብ 45 ከመቶ፤ ኢኮኖሚ ደግሞ 35 በመቶውን ይይዛሉ
16ኛው የብሪክስ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በሩሲያ ይጀመራል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በጉባኤው ለመሳተፍ ካዛን ከተማ መግባታቸውን ታስ የዜና ወኪል አስነብቧል።
ከጥር ወር 2024 ጀምሮ ብሪክስንን ከተቀላቀሉት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድም ትናንት ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መክረዋል።
ለሶስት ቀናት በካዛን የሚካሄደው ጉባኤ ባለብዙ ወገን ትብብርን የሚያጠናክሩ በርካታ ውይይቶች ይካሄዱበታል የተባለ ሲሆን፥ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትም አንዱ አጀንዳ ይሆናል።
ቻይና፣ ህንድ፣ ብራዚል እና ብሪክስን በቅርቡ የተቀላቀሉት እንደ ኤምሬትስ ያሉ ሀገራት ፕሬዝዳንት ፑቲን የዩክሬኑን ጦርነት እንዲያቆሙ ጥሪ በማድረግ ላይ ናቸው።
በምዕራባውያን ጦርነት ታውጆብኛል፤ አሜሪካ መራሾ ኔቶም የጦር ወንጀለኛ ነው ሲሉ የሰነበቱት ፑቲን ለብሪክስ አባል ሀገራት ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሩሲያ የተያዙ የዩክሬን ግዛቶች በፍጹም አይመለሱም ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የዩክሬንን 20 በመቶ የሚጠጋ መሬት የያዘችው ሞስኮ በምስራቃዊ ዩክሬን የተቆጣጠረቻቸውን አራት ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ የግዛቷ አካል ማድረጓን በማውሳትም ከኬቭ ጋር የሚደረግ ንግግር ይህንን የሚሽር አይሆንም ብለዋል።
በብሪክስ ጉባኤ ዋዜማ ከፑቲን ጋር የመከሩት የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ሶስተኛ አመቱን ሊይዝ የተቃረበውን ጦርነት ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ዘጠኝ ጊዜ የእስረኞች ልውውጥ እንዲያደርጉ የተሳካ የማደራደር ሚና የተወጣችው አቡ ዳቢ፥ ኬቭ እና ሞስኮን ለማቀራረብ የጀመረችውን ጥረት ቻይና እና ህንድም እንደሚደግፉት ይጠበቃል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንዳራ ሞዲ በካዛኑ ጉባኤ የሚሳተፉ ሲሆን፥ የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በገጠማቸው ህመም ወደ ሩሲያ አያቀኑም ተብሏል።
ግዙፉ ባለብዙ ወገን ስብስብ - ብሪክስ
“ብሪክ” (BRIC) የሚለውን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው ብሪታኒያዊው የኢኮኖሚ ባለሙያ ጂም ኦኔይል ነው።
ከብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ቻይና ስያሜ የመጀመሪያ ፊደል ወስዶ “ብሪክ” የሚለውን ስያሜ ሲሰጥ በ21ኛው ክፍለዘመን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚያስመዘግቡ ሀገራት መሆናቸውን በመጥቀስ ነው።
የአራቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በፈረንጆቹ 2006 ሃምሌ ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ምክክር አድርገዋል።
“ብሪክ” የሚለው ስያሜ ጥቅም ላይ የዋለው ግን ሚኒስትሮቹ በመስከረም ወር 2006 ከመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በኒውዮርክ ምክክር ሲያደርጉ ነው።
የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤም በሰኔ ወር 2009 በሩሲያ አስተናጋጅነት መካሄዱ ይታወሳል።
“ብሪክ” ወደ “ብሪክስ” ያደገው ደቡብ አፍሪካ በ2010 በይፋ ቡድኑን ተቀላቅላ በ2011 የመጀመሪያው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ስትሳተፍ ነው።
የአለማችን 40 በመቶ ህዝብ እና ከ30 በመቶ በላይ ኢኮኖሚ የሚይዙ ሀገራት ስብስብ የሆነው ብሪክስ አሁን ላይ 10 አባላት ያሉት ቡድን ሆኗል።
32 ሀገራትም የአለማችን 45 በመቶ ህዝብ፤ 35 በመቶ ኢኮኖሚ የሚይዘውን ቡድን ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረባቸውን ከሞስኮ የወጡ ዘገባዎች አመላክተዋል።