ቱርክ የአውሮፓ ህብረት ሙሉ አባል ካደረጋት ብሪክስን ላትቀላቀል እንደምትችል ገለጸች
ቱርክ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን በይፋ ከጠየቀች 40 ዓመት ሊሆናት ጥቂት ዓመት ብቻ ይቀራታል
የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ለማቅረብ እየተዘጋጀች መሆኗን ገልጻለች
ቱርክ የአውሮፓ ህብረት ሙሉ አባል ካደረጋት ብሪክስን ላትቀላቀል እንደምትችል ገለጸች።
በአውሮፓ እና እስያ አህጉራት መካከል የምትገኘው ቱርክ በፈረንጆቹ 1987 ላይ ነበር የአውሮፓ ህብረትን በአባልነት ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበችው።
በፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶሀን የምትመራው ቱርክ አውሮፓ ህብረትን የመቀላቀል ጥያቄዋ እስካሁን አልተሳካም።
ይህን ተከትሎ የብሪክስ ስብስብን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆኗ ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት የቱርክ ብሪክስን ልቀላቀል ጥያቄ እንዳሳሰበው ሲገለጽ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶም አባሉ የአንካራ ብሪክስን ለመቀላቀል ማሰቧ እንዳሳሰበው ሲገለጽ ቆይቷል።
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፊዳን ሀካን በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚንስትሩ ከቱርክ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ "ቱርክ የአውሮፓ ህብረትን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘ ብሪክስን ላትቀላቀል ትችላለች" ብለዋል።
ሚንስትሩ አክለውም "ቱርክን ጨምሮ ማንኛውም ሀገር የፈለገውን ጥምረት የመቀላቀል መብት አለው" ሲሉም ተናግረዋል።
አንካራ የአውሮፓ ህብረትን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት የማያገኝ ከሆነ ከብሪክስ በተጨማሪ የደቡድ ምስራቅ እስያ ሀገራትን ልትቀላቀል እንደምትችል ሚንስትሩ ተናግረዋል።
የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ጥምረት የሆነው ብሪክስ ከአንድ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ፣ አረብ ኢምሬት፣ ግብጽ እና ኢራንን በአባልነት መቀበሉ አይዘነጋም።