የኡጋንዳ ፖሊስ ሙሽሪት በሰርግ ላይ ሳለች በቁጥጥር ስር አውለዋል ባላቸው አባላቱ ላይ ክስ መሰረተ
ፖሊስ ሙሽሪት “በህይወቷ ውስጥ በጣም ደስተኛ መሆን የነበረባት ቀን በቅዠት መጠናቀቁ ያሳዝናል” ብሏል
የኡጋንዳ ፖሊስ ድርጊቱን በመፈጸም የተከሰሱት ፖሊሶች ከስራ እስከመሰናበት የሚያደርስ ቅጣት ሊበየንባቸው ይችላል ብሏል
የኡጋንዳ ፖሊስ፤ በስርቆት የተጠረጠረችው ሙሽሪትን በሰርግ ላይ ሳለች በቁጥጥር ስር አውለዋል ባላቸው አባላቱ ላይ ክስ መሰረተ፡፡
ክስ ከተመሰረተባቸው ፖሊሶች በቁጥጥር ስር የዋለው አንድ የፖሊስ መኮንን በእስር ላይ ሲሆን ሌሎቹ ተደብቀው እንደሚገኙ የኡጋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፍሬድ ኤናንጋ ተናግረዋል።
አራቱ ሰዎች የተከሰሱት ከፖሊስ የማይጠበቅና ያልተገባ ባህሪይ ማሳየት በሚል ሲሆን፤ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከፖሊስነት ስራቸው እንዲባረሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ቃል አቀባዩ አስታውቋል፡፡
ቃል አቀባዩ ኤናንጋ በሰጡት መግለጫ “በህይወቷ ውስጥ በጣም ደስተኛ መሆን የነበረባት ቀን በቅዠት መጠናቀቁ ያሳዝናል”ም ብለዋል።
በሙሽሪት ላይ የተመሰረተው የስርቆት ክስ የቀድሞ አሰሪዋ የባንክ ወኪል ሆና ስትሰራ በነበረችበት ወቅት ያቀረበችውን ቅሬታ ተከትሎ የመጣ እንደሆነ ተገልጿል።
ከዚህም በዘለለ ከሳሽና ተከሳሽ የሲቪል መፍትሄ በመፈለግ ጉዳያቸው እንዲዘጉ ባለፈው ወር ሶስተኛ አካል ባለበት ከስምምነት መድረሳቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለእስር ባበቃው ምክንያት ያዘኑት ቃል አቀባዩ፤ ሙሽሪትን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ድርጊት "የሚወገዝ እና ደካማ ፍርድ ላይ የተመሰረተ ነው" ብለውታል።
ሙሽሪት ቅዳሜ ምሽት ከታሰረች በኋላ በምእራብ ዩጋንዳ ምባራራ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዳ ለአንድ ሌሊት ከቆየች በኋላ እሁድ እለት መፈታቷ ዘ-ስታር ዘግቧል።