የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ባለቤት ብሪጅት ማክሮን ጾታቸው ወንድ ነው ብለው ዘገባ የሰሩ ጋዜጠኞች 8 ሺህ የሮ ካሳ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው
ሁለቱ ጋዜጠኞች ብሪጅት ማክሮን ፕሬዝዳንት ማክሮን ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲሰሩ እንደቆዩ ተገልጿል
ጋዜጠኞቹ ያልተረጋገጠ እና ሐሰተኛ ዘገባ ሰርተዋል በሚል ጥፋተኛ ተብለዋል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ባለቤት ብሪጅት ማክሮን ጾታቸው ወንድ ነው ብለው ዘገባ የሰሩ ጋዜጠኞች 8 ሺህ የሮ ካሳ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው።
የ71 ዓመቷ የፈረንሳይ ቀዳማዊ እመቤት በሙያቸው መምህር የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ባንድ ወቅት ከተማሪዎቻቸው አንዱ የሆኑት ኢማኑኤል ማክሮንን አግብተዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ለቀድሞ መምህሩ እና ለባለቤቱ አክብሮት እና ፍቅር እንዳለው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በፈረንሳይ የዩቲዩብ ጋዜጠኛ የሆኑ ሁለት ጋዜጠኞች ቀዳማዊ እመቤት ብሪጅት ማክሮን በተፈጥሮ ወንድ እንደነበሩ እና ጾታቸውን እንዳስቀየሩ ዘግበዋል።
ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ በተደጋጋሚ ተሰራጭቷል የተባለው ይህ ዘገባ ከወጣ በኋላ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን ቀዳማዊ እመቤቷም ስማቸው መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡
ቀዳማዊ እመቤቷ ከስም መጥፋት በተጨማሪም ሐሰተኛ ነው በተባለው በዚህ ዘገባ ምክንያት ለፖለቲካ ሴራም ተጋልጫለሁ ሲሉ ክስ መስርተዋል።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ዙሪያ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ችሎት የሰየመ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ክስ የቀረበባቸው ሁለት ጋዜጠኞች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሩሲያ ላይ ለምን አመረሩ?
እንደ ዘገባው ከሆነ ጋዜጠኞች የፕሬዝዳንት ማክሮን ባለቤት ብሪጅት ማክሮን ከመባላቸው በፊት ጂያን ማይክል የሚባሉ ወንድ እንደነበሩ ለችሎቱ ቢናገሩም ይህንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም ተብሏል።
ጋዜጠኞቹ አሰራጭተውታል በተባለው ዘገባ ምክንያት በቀዳማይ እመቤቷ ላይ ለደረሰው የስም ማጥፋት ወንጀል 10 ሺህ ዩሮ ካሳ እንዲከፈላቸው ችሎቱን ጠየቁ ቢሆንም ጋዜጠኞቹ 8 ሺህ ዩሮ ለተጎጂዎች እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል።
በአውሮፓ እና አሜሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች ላይ መሰል ስም ማጥፋት ዘገባዎች ሲሰሩ የብሪጅት ማክሮን የመጀመሪያው ሳይሆን በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማ ላይም ተመሳሳይ ዘገባዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
እንዲሁም በቀድሞ የስዊዘርላንድ ፕሬዝዳንት ጃሲንዳ አርደን ላይም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ዘገባዎች ሲሰራጩ ቆይተዋል።