የአውሮፓ አየር ክልል ከአሜሪካ ተጽዕኖ መውጣት እንዳለበት ፕሬዝዳንት ማክሮን ገለጹ
አውሮፓ የአየር ክልሏን በራሷ መጠበቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ሊኖራት እንደሚገባም ተገልጿል
የፓሪስ ዓለም አቀፍ የአየር ትርኢት በመካሄድ ላይ ነው
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአውሮፓ የአየር ክልል ከአሜሪካ ተጽዕኖ መውጣት እንዳለበት ገለጹ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በፓሪስ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የአየር ትርኢት መክፈቻ አውደርዕይ ላይ ባደረጉት ንግግር አውሮፓ የአየር ክልሏን በራሷ መጠበቅ መቻል አለባት ነው ያሉት፡፡
አውሮፓዊያን የአየር ክልላቸውን በአሜሪካ ሰራሽ የመከላከያ ጦር መሳሪያዎች በመጠበቅ ላይ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንት ማክሮን ይህ ጥገኝነት ግን ሊያበቃ ይገባል ብለዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደች ያለው ጦርነት ለአውሮፓ ጥሩ ምሳሌ ነው የሚሉት ፕሬዝዳንቱ አውሮፓ የራሷን የአየር ላይ መከላከያ ስርዓት ልትገነባ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
“ስጋቶቻችን ምን እንደሆኑ በራሳችን ልናውቅ ይገባል፣ እንደዛ ስናደርግ ምን እንደሚያስፈልገን እና እንዴት ችግራችን እንደምንፈታ ማወቅ አለብን" ማለታቸውንም ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የአውሮፓ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች የአውሮፓን አየር ክልል ከየትኛውም ጥቃት መጠበቅ የሚያስችሉ ቴኬኖሎጂዎችን እንዲያመርቱ መደገፍ እንደሚገባም ፕሬዝዳንት ማክሮን ጠቅሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም አውሮፓ የራሷን የአየር ክልል በራሷ ለመጠበቅ የጦር መሳሪያ ማምረት መጀመሯን በዩክሬን በሙከራ ላይ እንዳለም ተናግረዋል፡፡
በፈረንሳይ እና በጣልያን ኩባያዎች የተሰራው "ማምባ" ጸረ ሚሳኤል ሲስተም ዩክሬን ከሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ጥቃት እየመከተችበት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በፓሪስ እየተካሄደ ባለው በዚህ ዓለም አቀፍ የአየር ትርኢት ለዩክሬን እና ሩሲያ አዋሳኝ የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት እየተሳተፉበት ነው ተብሏል፡፡
ጀርመን የአውሮፓን የአየር ክልል ከጥቃት ለመጠበቅ ከ17 ሀገራት በላይ የተሳተፉበት ቡድን ያዋቀረች ሲሆን ፈረንሳይ ግን የጀርመንን ድርጊት ተቃውማለች፡፡
ፈረንሳይ በጀርመን የተዋቀረው የአውሮፓ አየር ክልል ጥበቃ ቡድንን ያልተቀላቀለችው በአሜሪካ እና እስራኤል ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሰረተ ነው በሚል እንደሆነ ተገልጿል፡፡