ማክሮን መጀመሪያ ከተመረጡበት ከ2017 ወዲህ ፈረንሳይ ከዘርማጥፋቱ በፊት እና በኋላ የነበራትን ሚና የሚዘረዝር ጥናት አስጠንተዋል
ፈረንሳይ እና አጋሮቿ በ1994 በሩዋንዳ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ማስቆም ይችሉ እንደነበረ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ገለጹ።
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጽ/ቤት እንዳስታወቀው ማክሮን ሩዋንዳ የዘርማጥፋቱን በምታስብበት በቀጣይ እሁድ የቪዲዮ መልእክት በማህበራዊ ሚዲያ ይለቃሉ።
- የ25 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የነበሩት የ"ሆቴል ሩዋንዳ" ጀግና ከእስር ተለቀቁ
- የብራዚሉ ፕሬዝደንት የጋዛውን ጦርነት ናዚ ከፈጸመው ዘርማጥፋት ጋር ማነጻጸራቸው እስራኤልን ክፉኛ አስቆጣ
በዚህ ቪዲዮ "ፈረንሳይ ከምዕራባውያን እና ከአፍሪካ አጋሮቿ ጋር ሆና ማስቆም ትችል የነበረ ቢሆንም ፍቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች" ማለታቸውን ፍራንስ24 ዘግቧል።
ማክሮን በ2021 የማዕከላዊ አፍሪካዊቷን ሀገር ሩዋንዳን በጎበኙበት ወቅት በአብዛኛው ቱትሲዎች እና ጥቃቱን ለመከላከል የሞከሩ ለዘብተኛ ሁቱዎች ለሞቱበት የዘርማጥፋት ወንጀል "ኃላፊነት" እንደሚወስዱ መናገራቸው ይታወሳል።
በሚዲያ በተደገፈው የዘርማጥፋት ዘመቻ 800ሺ ሰዎች ተገድለዋል።
ፕሬዝደንቱ ይቅርታ ባይጠይቁም የሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ፈረንሳይ ግንኙነት ለማደስ ተከታታይ ጥረት ካደረገች በኋላ የፈረንሳይ-ሩዋንዳ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ማለታቸው ይታወሳል።
ማክሮን መጀመሪያ ከተመረጡበት ከ2017 ጀምሮ ፈረንሳይ ከዘርማጥፋቱ በፊት እና ወቅት የነበራትን ሚና የሚዘረዝር ጥናት አስጠንተዋል።
እሁድ ይለቀቃል በተባለው ቪዲዮ ፕሬዝደንቱ የዘርማጥፋቱ ሲጀመር አለምአቀፉ ማህበረሰብ እርምጃ መውሰድ የሚችልበት መረጃ እንደነበረው ያነሳሉ።
ማክሮን "ቱትሲ በመሆናቸው ብቻ የተሰውትን አንድ ሚሊዮን ህጻናት፣ ሴቶች፣ እና ወንጆች በማሰብ ፈረንሳይ ከሩዋንዳ እና ከሩዋንዳ ህዝብ ጎን ትቆማለች"ብለዋል።