ሩሲያ በበኩሏ ፈረንሳይ ከቀድሞ ቅኝ ግዛት ሀገራት ፊት መንሳት ጀርባ የሞስኮ እጅ አለበት ብላ በማሰቧ ነው ብላለች
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሩሲያ ላይ ለምን አመረሩ?
ሶስተኛ ዓመቱን በያዘው ዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ የሚገኝ ሲሆን ዩክሬንን በጦር መሳሪያ ሲረዱ የነበሩት የኔቶ አባል ሀገራት አሁን ላይ ወታደሮችን እንላክ የሚል ክርክር ላይ ናቸው፡፡
የሀሳቡ አመንጪ የሆነችው ፈረንሳይ ስትሆን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሀገራቸው ወደ ዩክሬን ወታደሮችን ልትልክ ትችላለች ብለዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱን አስተያየት ተከትሎ በርካቶች የፕሬዝዳንቱን አስተያየት ውድቅ ያደረጉ ሲሆን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን (ኔቶ) ወታደሮቹን ወደ ዩክሬን እንደማይልክ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያዊው ቅጥረኛ ወታደር ከዩክሬን ጎን ሆኖ ሩሲያን እየተዋጋ እንደሆነ ተገለጸ
ፕሬዝዳንት ማክሮን አሁንም በዚህ ሀሳባቸው የጸኑ ሲሆን በምክንያትነት ያስቀመጡት ደግሞ የዩክሬን መሸነፍ ለአውሮፓ ስጋት በመሆኑ፣ ሩሲያ በፈረንሳይ ጥቅሞች ላይ ጥቃት በመሰንዘሯ እና አውሮፓ ደህንነቱን በራሱ ማስከበር አለበት በሚል መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፈረንሳይ በሩሲያ ላይ ጥቃት መሰንዘር እና ጦርነትም አትፈልግም ያሉት ፕሬዝዳንት ማክሮን ነገር ግን ፕሬዝዳንት ፑቲን የኑክሌር ጦርነት እንደሚጀምሩ እያስፈራሩ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከኔቶ በተጨማሪም ጀርመንን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ዩክሬን እንደማይልኩ የገለጹ ሲሆን ፕሬዝዳንት ማክሮን ሀሳባቸውን እንደሚገፉበት ሀገራትንም ለማሳመን እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ፈረንሳይ ይህንን የምታደርገው ለዪክሬን አስባ እንዳልሆነ የቀድሞ ቅኝ ተገዢ ሀገራት ፊት ስለነሷት ለዚህ ደግሞ ከጀርባ ሞስኮ እጇ አለበት ብላ ስለምታምን ነው ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ፈረንሳይ ከምዕራብ አፍሪካዎቹ ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ጋር ያላት ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እየመሰሩ መሆናቸውን ሀገራቱ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ የደህንነት ጥቃት ከተሰማት የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿን እንደምትጠቀም ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡