የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ባለቤት ብሪጅት ማክሮን ጾታቸውን አስቀይረዋል ያሉ ጋዜጠኞች ላይ ክስ መሰረቱ
ሁለት ጋዜጠኞች የፕሬዝዳንት ማክሮን ባለቤት በተፈጥሮ ወንድ እንደነበሩ ባደረጉት የምርመራ ዘገባ አረጋግጠናል ብለዋል
በዘገባው ምክንያት ስሜ በአውሮፓ እና አሜሪካ ጠፍቷል ያሉት ቀዳማዊ እመቤቷ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ባለቤት ብሪጅት ማክሮን ጾታቸውን አስቀይረዋል ያሉ ጋዜጠኞች ላይ ክስ መሰረቱ።
የ71 ዓመቷ የፈረንሳይ ቀዳማዊ እመቤት በሙያቸው መምህር የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ባንድ ወቅት ከተማሪዎቻቸው አንዱ የሆኑት ኢማኑኤል ማክሮንን አግብተዋል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ለቀድሞ መምህሩ እና ለባለቤቱ አክብሮት እና ፍቅር እንዳለው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
በፈረንሳይ የዩቲዩብ ጋዜጠኛ የሆኑ ሁለት ጋዜጠኞች ቀዳማዊ እመቤት ብሪጌት ማክሮን በተፈጥሮ ወንድ እንደነበሩ እና ጾታቸውን እንዳስቀየሩ ዘግበዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት ተሰራጭቷል የተባለው ይህ ዘገባ ከወጣ በኋላ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን ቀዳማዊ እመቤቷም ስማቸው መጥፋቱን እና በዘገባው ምክንያት ለፖለቲካ ሴራም ተጋልጫለሁ ሲሉ ክስ መስርተዋል።
የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት ጉዳዩን መመልከት የጀመረ ሲሆን ክስ የቀረበባቸው ሁለት ጋዜጠኞች እና የቀዳማዊ እመቤቷ ጠበቃ ችሎት እንደቀረቡ ፍራንስ 24 ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ጋዜጠኞች የፕሬዝዳንት ማክሮን ባለቤት ብሪጅት ማክሮን ከመባላቸው በፊት ጂያን ማይክል የሚባሉ ወንድ እንደነበሩ ለችሎቱ ተናግረዋል ተብሏል።
ጋዜጠኛዋ አክላም በጉዳዩ ዙሪያ ለሶስት ዓመታት ምርመራ ስታደርግ ከቆየች በኋላ እርግጠኛ ስትሆን ዘገባውን እንደሰራችም ተናግራለች።
የቀዳማዊ እመቤት ብሪጅት ማክሮን ጠበቃ በበኩላቸው ጂያን ማይክል ተብሎ የሚጠራው ሰው የብሪጅት ማክሮን ወንድማቸው መሆኑን እንደተናገረ ተገልጿል።
ጋዜጠኞቹ አሰራጭተውታል በተባለው ዘገባ ምክንያት በቀዳማይ እመቤቷ ላይ ለደረሰው የስም ማጥፋት ወንጀል 10 ሺህ ዩሮ ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል ተብሏል።
በአውሮፓ እና አሜሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች ላይ መሰል ስም ማጥፋት ዘገባዎች ሲሰሩ የብሪጅት ማክሮን የመጀመሪያው ሳይሆን በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባለቤት ሚሼል ኦባማ ላይም ተመሳሳይ ዘገባዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
እንዲሁም በቀድሞ የስዊዘርላንድ ፕሬዝዳንት ጃሲንዳ አርደን ላይም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ዘገባዎች ሲሰራጩ ቆይተዋል።