ብሪስባን ከሚልቦርን እና ሲዲኒ በመቀጠል ኦሎምፒክ ለማዘጋጀት የተመረጠች ሶስተኛዋ የአውስትራሊያ ከተማ ትሆናለች
የአውስትራሊዋ ብሪስባን ከተማ ከ10 ዓመት በኋላ በፈረንጆቹ በ2032 የሚካሄደውን ኦሊምፒክ እንድታዘጋጅ መመረጧን የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ኮሚቴው ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ጎን ለጎን ባደረገው ጉባዔ የአውስትራሊያዋ ብሪስባን ከተማ 35ኛውን ኦሊምፒክ እንድታዘጋጅ ወስኗል፡፡ የኮሚቴው ፕሬዝዳንት ቶማስ ባችም ይህንኑ በጃፓን መዲና ቶኪዮ አብስረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ብሪስባን ከተማ፤ ከሚልቦርን እና ሲዲኒ በመቀጠል ኦሊምፒክ ያዘጋጀች ሶስተኛዋ የአውስትራሊያ ከተማ ትሆናለች፡፡
የ2024 ኦሊምፒክ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የ 2028 ደግሞ በአሜሪካ ሎስአንጀለስ እንደሚደረግ ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ሊካሄድ የነበረው ቶኮዮ ኦሎምፒክ 2020 በአለም ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ወረርሸኝ ምክንያት መራዘሙ ይታወሳል፡፡ በወረርሽኑ ምክንያት የተራዘመው ቶኪዮ ኦሎምፒክ2020 በዚህ ወር ይጀመራል፡፡