በብሪታኒያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ እየተሰጠ ነው
በምርጫው የወግ አጥባቂው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የሌበሩ ጄሬሚ ኮርቢን፣ የሊበራል ዴሞክራቷ ጆ ሰዊንሰን እንዲሁም የሶሻል ዴሞክራቱ ስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲ ኒኮላ ስተርጂን ይፎካከራሉ፡፡
በእንግሊዝ፣ በዌልስ፣ በስኮትላንድና በሰሜናዊ አየርላንድ በሚገኙ 6 መቶ 50 ምርጫ ክልሎች ድምጽ መስጫዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
ምርጫ ጣቢያዎቹን ወክለው አብላጫ ድምጽ የሚያገኙ 6 መቶ 50 እጩዎችም ምክር ቤቱን በአባልነት ይቀላቀላሉ፡፡
ምርጫው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10፡00 ላይ የተጀመረ ሲሆን ነገ ጠዋት (አርብ) 1 ሰዓት ላይ ይጠናቀቃል፡፡ ድምጽ ቆጠራው ወዲያውኑ የሚጀመር ሲሆን አሸናፊዎች በእለቱ እንደሚታወቁ ይጠበቃል፡፡
በ2017ቱ ምርጫ የማዕከላዊ ኒውካስል ምርጫ ጣቢያ አሸናፊ ነበር ቀድሞ የተገለጸው፡፡
ብሪታኒያ እንዲህ ዓይነቱን ሃገር አቀፍ ምርጫ በየ4 ወይም በየ5 ዓመት ልዩነት ነበር የምታደርገው፡፡
የአሁኑ ግን በባለፉት አምስት አመታት ውስጥ ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡
በሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት የሃገሪቱ ፓርላማ አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ቅድመ ምርጫ ድምጽ ሰጥተው እንደነበርም ይታወሳል፡፡
ይህ ሃገራዊ ምርጫ ቴሬሳ ሜይን ተክተው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር በተቆናጠጡት ቦሪስ ጆንሰን ጥሪ የሚካሄድ ነው፡፡
የብሬግዚት (የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመነጠል ሂደት) ጉዳይ በፓርላማ ውሳኔ ማግኘት አለመቻሉ ቦሪስ ይህን እንዲያደርጉ እንዳስገደዳቸውም ይነገራል፡፡
ቦሪስ በማዕከላዊ ሎንደን፣ኮርቢን በሰሜናዊ ሎንደን፣ኒኮላ ስተርጂን እና ጆ ሰዊንሰን ደግሞ በስኮትላንድ ግላስጎ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
የድምጽ አሰጣጡ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ እና በፖስታ የሚካሄድ ነው፡፡
የብሬግዚት ፓርቲ መሪው ኒጌል ፋራዥ በፖስታ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡