“ፍቅርና ወንድማማችነትን በማጠናከር በተባበረ መንፈስ ሃገራችንን እናበልጽግ”፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሱ ጊዜ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ ፍቅርና ወንድማማችነትን በማጠናከር በተባበረ መንፈስ ሃገራችንን ለማበልጸግ ልንተጋ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ኮሚቴው ያወቀውን ቢሸልምም ሽልማቱ ለሁላችንም የተሰጠ ነው ”ያሉት ዐቢይ (ዶ/ር) ፣አጋጣሚውን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በመነሻነት ልንወስደው ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አያይዘውም ኢትዮጵያ ውስጥ ትውልድ የሚበላ ሾተላይ አለ ያሉ ሲሆን ወደ መሰላል የሚወጡትን የሚበላውን ይህን ሾተላይ በማከም መደገፉ ለሁሉም እንደሚበጅ ነው የተናገሩት፡፡ መሰላል የሚወጡትን ጎትቶ ከማውረድ ይልቅ ከጫፍ እንዲደርሱ ልንደግፍ ይገባልም ብለዋል፡፡
ብዙዎች የተከታተሉት የሽልማት ስነስርዓቱ የኢትዮጵያና የኤርትራን ብሎም የቀጣናውን ገጽታ በመቀየር ረገድ የጎላ አበርክቶ ያለው በመሆኑ አጋጣሚውን በመጠቀም በተባበረ ክንድ ወደ ብልጽና ልንሸጋገርበት ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመላው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ እንዲሁም ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የእንኳን ደስ ያላችሁና የምስጋና መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በተለየ መንገድ ካመሰገኗቸው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በቅርቡ ተገናኝተው በጋራ ሊያከብሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
100ኛውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሸነፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኖርዌይ አስሎ ሽልማታቸውን በደማቅ ስነስርዓት መቀበላቸው ይታወሳል፡፡ 900,000 የአሜሪካ ዶላርም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት አካል ነው፡፡