ኢትዮጵያ በሚቀጥለዉ ሳምንት የምታመጥቀዉ ሳተላይትየግብርና ምርትን ለማሳደግ ይጠቅማል ተባለ
ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቋ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እንድታሳድግ ያግዛታል ሲሉ የግብርና ዘርፍ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማምጠቅ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቶታል። የሳተላይቷ መምጠቅ ሀገሪቱ ለመረጃ ግዢና ለሌሎች አገልግሎቶች የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስቀርላት ና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የዘርፉ ባለሙያዎች ለኢዜአ እንደገለጹት የሳተላይት ቴክኖሎጂው የግብርና ዘርፍን ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል፡፡
በሚኒስቴሩ የዘርፉ ባለሙያ አቶ ወንድወሰን ካሳሁን እንደተናገሩት የሳተላይት ቴክኖሎጂ በአሜሪካና እንግሊዝ የኢኮኖሚያ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ የተመሰረቱ ታዳጊ ሀገራት የሳተላይት ቴክኖሎጂ እድገታቸውን ለማፋጠን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂውን መጠቀሟ የግብርና የምርት ብክነትን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ነው ያሉት።
“በአገሪቱ 1/3ኛው የሆነው ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት ይባክናል” ያሉት ባለሙያው የሳተላይት ቴክኖሎጂው ቀድሞ የደረሱ ምርቶችን በመለየት ከመባከኑ በፊት እንዲሰበሰብ መረጃ በመስጠት ያግዛል ብለዋል።
ቴክኖሎጂው ፈጣንና አስተማማኝ መረጃ በመስጠት ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችል ገልጸው፤ የአንበጣ መንጋ ና ሌሎች በግብርና ምርት ላይ የሚደርሱ ችግሮችን አስቀድሞ በመተንበይ ለመከላከል እንደሚረዳም ጠቅሰዋል።
በግብርና ሚኒስቴር ሌላው የዘርፉ ባለሙያ አቶ አለማየሁ መኮንን በበኩላቸው የሳተላይት ቴክኖሎጂ ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ መረጃዎችን በፍጥነት በመስጠት ለግብርና ምርትና ምርታመነት ጉልህ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
አርብቶ አደሩ ግጦሽና ውሀ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በሚዘዋወርበት ወቅት በቂና ወቅታዊ መረጃ ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸው፤ የከርሰ ምድር ሀብትን በመለየት በተለይም የትኛው መሬት ውሀ እንዳለውና ለምን አገልግሎት መዋል እንደሚችል በመለየት በኩልም ሚናው የጎላ መሆኑን ነው አቶ አለማየሁ የገለጹት።
በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት መዛባት በመኖሩ ዝናብና ጸሀይ ወቅቱን ጠብቆ የማይመጣ በመሆኑ የሳተላይት ቴክኖሎጂው ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃ በመስጠት አስፈላጊውን የግብርና ሥራ ዝግጅት ለማድረግ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅትማጠናቀቋን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል።
ምንጭ፡- ኢዜአ