ብሪታንያ ከስድስት ዓመት በፊት አውሮፓ ህብረትን መልቀቋ ይታወሳል
ብሪታንያ አዲስ የአውሮፓ ሀገራት ስብስብን ልትቀላቀል እንደምትችል ገለጸች
የወቅቱ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚመሩት የአውሮፓ የፖለቲካ ማህበረሰብ የሚባል ስብስብ ያለ የፊታችን ጥቅምት በቼክ ሪፐብሊክ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ከስድስት ዓመት በፊት በህዝበ ውሳኔ ከአውሮፓ ህብረት የለቀቀችው ብሪታንያ በዚህ መድረክ ላይ ልትካፈል እንደምትችል አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ይህ የአውሮፓ የፖለቲካ ማህበረሰብ መድረክ በደህንነት፣ ሀይል ልማት፣ ትራንስፖርት እና በሰዎች ነጻ እንቅስቃሴ ዙሪያ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡
ይህ መድረክ ዋነኛ ዓላው በአውሮፓ ሀገራት መካከል የበለጠ መቀራረብ እና ለጋራ ጉዳዮች እንዲሰራ ማበረታታት ችግሮችን መፍታት ቢሆንም ብሪታንያ ግን መድረኩ በአውሮፓዊያን ብቻ እንዲታጠር እንደማትፈልግ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት በዚህ መድረክ ላይ ከአውሮፓ ሀገራት ውጪ ያሉ ሀገራት የሚሳተፉ ከሆነ ብሪታንያ መድረኩ ላይ በደስታ እንደምትካፈል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በተለይም በዚህ መድረክ ላይ ከአውሮፓ ህብረት በተጨማሪ ቱርክ፣ ዩክሬን፣ ኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ፣ አይስላንድ፣ አርመኒያ፣ ጆርጂያ፣ ሞልዶቫ እና አዛርባጂያን እንዲገኙ ይጋበዛሉም ተብሏል፡፡
ይሁንና በዚህ መድረክ ላይ ዋነኛ አጀንዳ ይሆናሉ ተብለው ከተለዩ ጉዳዮች መካከል የአውሮፓ ሀገራት የነዳጅ እጥረት እና የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ተጠባቂዎቹ ናቸው፡፡
እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት እያለ እንደዚህ አይነት መድረክ ለምን ይዘጋጃል የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ሲሆን በተለይም በቀጣይ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን የሚጠይቁ ሀገራትን ቁጥር ሊቀንሰው ይችላል እየተባለ ይገኛል፡፡