የብሪታንያው ፓውንድ በ37 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ዝቅተኛ የመግዛት አቅም አስመዘገበ
የአውሮፓ ህብረት መገበያያ ዩሮ በ20 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከዶላር በታች ተመንዝሯል
የሩሲያው ሩብል ደግሞ ከሰባት ዓመት በኋላ መነቃቃት አሳይቷል ተብሏል
የብሪታንያው ፓውንድ በ37 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ዝቅተኛ የመግዛት አቅም አስመዘገበ፡፡
የአሜሪካ ዶላር፣ የአውሮፓ ህብረት ዩሮ፣ የብሪታንያ ፓውንድ ስተርሊንግ ፣ የቻይናው ዩዋን እና የሩሲያው ሩብል በዓለማችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ዋነኛ መገበያያ ገንዘቦች ናቸው፡፡
ከእነዚህ መገበያያ ገንዘቦች ጀርባ ሀገራቱ ያሉ ሲሆን የዓለምን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠርም የንግድ ፉክክሩ በእነዚሁ ሀገራት መካከል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመራች በኋላ የዓለም ንግድ እና ዲፕሎማሲ መዛነፍ ገጥሞታል፡፡
በአሜሪካ አስተባባሪነት በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እና ሩሲያ በማዕቀቡ ላለመጎዳት የወሰደቻቸው የአጸፋ እርምጃዎች በዓለም ምግብ እና ነዳጅ ላይ ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግ አስገድዷል፡፡
በዚህም ምክንያት የአውሮፓ ህብረት ሀገራት መካከል የጋራ መገበያያ የሆነው ዩሮ ከሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በፊት ከዶላር በላይ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ከጦርነቱ በፊት አንድ ዩሮ ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር የዜሮ ነጥብ 14 ብልጫ የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት አንድ ዩሮ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር የዜሮ ነጥብ 33 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ይህም ዩሮ ከአሜሪካ ጋር ሲነጻጸር የመግዛት አቅሙ ከ20 ዓመት በኋላ ቅናሽ ማሳየቱ ሲገለጽ ለዩሮ አቅም መዳከም ደግሞ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በሞስኮ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ተከትሎ በአውሮፓ ያጋጠመው የነዳጅ እጥረት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የብሪታንያ ፓውንድ ስተርሊን ደግሞ በ37 ዓመት ታሪክ ውስጥ የታየ ታሪካዊ የመግዛት አቅም መዳከም እንደሆነ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የብሪታንያ ብሄራዊ ስታስቲክስ ቢሮ እንዳለው ከሆነ አንድ ፓውንድ በ1 ነጥብ 14 ዶላር እየተመነዘረ ሲሆን ይህም ከፈረንጆቹ 1985 ጀምሮ ዝቅተኛው ሆኖ ተመዝግቧል ተብሏል፡፡
ፓውንድ ስተርሊን ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ብልጫ እንዲሁም ከዩሮ ጋር ደግሞ የ12 በመቶ ብልጫ እንደተወሰደበት በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የሩሲያው ሩብል ደግሞ ከፈረንጆቹ 2015 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዶላር ጋር ያለውን ልዩነት ያጠበበ ሲሆን ሞስኮ ነዳጇን በሩብል ለመሸጥ መወሰኗ እና ለእስያ ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ መሸጧ ለመገበያያ ገንዘቧ ማገገም ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
አሁን ላይ አንድ የአሜሪካን ዶላር በ60 ነጥብ 8 የሩሲያ ሩብል በመመንዘር ላይ የሚገኝ ሲሆን በአውሮፓ አሁንም የነዳጅ እጥረቱ የቀጠለ በመሆኑ የዩሮ እና ፓውንድ ስተርሊንግ አቅም እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችል ተገምቷል፡፡