ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የጠየቁት የብሪታንያ ወደብ ሰራተኞች የስምንት ቀናት አድማ መቱ
ሰራተኞቹ ያደሙበት ፌሊክስቶው ወደብ ከብሪታንያ ትልቁ የወደብ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ነው
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ ያሻቀበ ሲሆን ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያዎችን እየጠየቁ ነው
የብሪታንያው ፌሊክስቶው ወደብ ላይ ሰራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የስምንት ቀናት አደማ መቱ።
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ጦርነት ማቅናታቸውን ተከትሎ የዓለም ነዳጅና ምግብ ዋጋ እያሻቀበ ሲሆን፤ ጦርነቱ የዓለምን የምርት አቅርቦት እና የዋጋ መዛነፍን አስከትሏል።
ሩሲያ 40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን ነዳጅ ፍላጎት የምትሸፍን ቢሆንም፤ ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦችን በመጣል ላይ ናቸው።
በዚህና ሌሎች ምክንያቶች በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ እና አቅርቦት በመጨመሩ ዜጎች መንግስቶቻቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ እርምጃዎች እንዲወስዱላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ይሄንን ተከትሎም በአውሮፓ የምርቶች ዋጋ ያሻቀበ ሲሆን ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያዎች እንዲደረግላቸው በተለያዩ መንገዶች በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
የብሪታንያው ፌሊክስቶው ወደብ አገልግሎት ሰራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርላቸው የስምንት ቀናት አድማ ያደረጉ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ 1 ሺህ 900 የወደቡ ሰራተኞች ስራ ማቆማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በብሪታንያ ካሉ የወደብ አገልግሎት ከሚሰጡ መሰል ተቋማት መካከል ትልቁ የሆነው የዚህ ተቋም ማሽን ኦፕሬተሮች፣ የክሬን አሽከርካሪዎች እና ሌሎች ሰራተኞች ስራ አቁመዋል ተብሏል።
በብሪታንያ ታሪክ ሰራተኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ተመሳሳይ አድማ ከመቱ 33 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ ዘንድሮ ኑሮ ተወዷል በሚል የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ፌሊክስቶው ወደብ በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር በ1875 የተመሰረተ ሲሆን፤ በዓመት ከአራት ሚሊየን በላይ ኮንቴይነሮችን ወይም ሁለት ሺህ መርከቦችን የማስተናገድ አቅም አለው።
በብሪታንያ ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው በአድማ ሲጠየቅ የአሁኑ የመጀመሪያው ያልሆነ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት የባቡር ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ከአንድ ወር በፊት ተመሳሳይ ነገር አድርገው ነበር።
በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች ወጪያቸውን ለመቀነስ በሚል የትምህርት ቀናትን አሁን ካለበት ወደ ሶስት ቀናት ዝቅ ለማድረግ ምክክር መጀመራቸው ባሳለፍነው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።
የጀርመኑ ግዙፍ የአቪየሽን ኩባንያ ሉፍታንዛ ሰራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርላቸው በጠሩት የስራ ማቆም አድማ ከአንድ ሺህ በላይ በረራዎቹን መሰረዙ አይዘነጋም።