ብሪታንያ የ”ደም ቅሌት” ተብሎ ለሚጠራው ስህተት 12 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ልትከፍል ነው
በብሪታንያ ከ40 ዓመት በፊት በተበከለ ደም ምክንያት 30 ሺህ ህዝብ በጉበት እና ኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ተጎድተዋል
የሀገሪቱ መንግስት ለተሰራው ስህተት በይፋ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ለተጎጂዎችም ካሳ እከፍላሉ ብሏል
ብሪታንያ የደም ቅሌት ተብሎ ለሚጠራው ስህተት 12 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ልትከፍል ነው፡፡
በ1970 ዎቹ እና 1980ቹ ላይ በብሪታንያ ጤንነቱ ያልተጠበቀ ደም እና የደም ውጤቶች በህክምና ተቋማት ህክምና ፈልገው ለመጡ ሰዎች ተሰጥቶ እንደነበር ዘግይቶ በተደረገ ምርመራ ተረጋግጧል፡፡
በዚህ ምርመራ ሪፖርት መሰረት በብሪታንያ እና ከአሜሪካ የተሰበሰቡ የደም ውጤቶች ለታካሚዎች በሚሰጥበት ወቅት ይህ ደም በሽታ አምጪ ቫይረሶችን ይዞ ተገኝቷል፡፡
ለታካሚዎች የተሰጠው ደም በርካቶችን ለኤችአይቪ እና ጉበት በሽታ አምጪ ቫይረስ እንዲጠቁ ይህም ለውስብስብ የጤና ችግሮች እንደዳረጋቸው ተረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ 30 ሺህ ገደማ ዜጎች በዚህ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ደም ተጎድተዋል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 3 ሺህ ያህሉ እንደሞቱ ምርመራው አስታውቋል፡፡
ብሪታንያ የኢትዮጵያ አበባ ያለ ግብር ወደ ሀገሯ እንዲገባ ፈቀደች
መንግስት ስህተት መስራቱን በማመንም ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንጆቹ 2015 ላይ በይፋ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን መንግስት ሀላፊነቱን እንዳልተወጣ በዚህ ምክንያትም ዜጎች እንደተጎዱ በይፋ ተናግረው ነበር፡፡
አሁን ስልጣን ላይ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ አስተዳድር ለተጎጂዎች 10 ቢሊዮን ፓውንድ ወይም 12 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ማቀዱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከዛሬ ጀምሮም የተጎዱ ዜጎች እና ካሳ የሚገባቸው ሰዎች ማንነት ይፋ እንደሚደረግ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡