በሙስና ቅሌት የተጠረጠሩ የዩክሬን ባለስልጣናት ከኃላፊነታቸው እየለቀቁ ነው
የሰራዊቱን የሎጅስቲክስ ድጋፍ ሲመሩ የነበሩት ምክትል ሚኒስትር ከለቀቁት ባለስልጣናት መካከል ይገኙበታል
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዘሌንስኪ ሰሞኑን ባደረጉት ንግግር “ሙስኞችን አንታገስም” ማለታቸው አይዘነጋም
ባለስልጣናቶቿ በከፍተኛ የሙስና ቅሌት ውስጥ የተዘፈቁባት ዩክሬን ሰሞኑን በሙሰኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ እውሰዳለው ማለቷ የሚታወቅ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዘሌንስኪ ባደረጉት ንግግር “ሙስኞችን አንታገስም!” ሲሉ መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
ይህን የፕሬዝዳንት ዘሌንሰኪ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር ተከትሎም በሙስና ቅሌት የተጠረጠሩ የዩክሬን ባለስልጣናት ከኃላፊነታቸው እየለቀቁ መሆኑ እየተዘገበ ነው፡፡
ባለስልጣናት እየለቀቁባቸው ካሉ መስሪያ ቤቶች ከምግብ (የዩክሬን ጦር ሎጂስቲክስ) ግዥ ቅሌት ጋር በተያያዘ ስሙ በስፋት እየተነሳ የሚገኘው የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አንዱ መሆኑ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊቱን የሎጅስቲክስ ድጋፍ ሲመሩ የነበሩት ምክትል ሚኒስትር ቭያቼስላቭ ሻፖቫሎቭ ከስልጣን መልቀቃቸውን አስታውቋል።
ምክትል ሚኒስተሩ ከስልጣን የለቀቁት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጋነነ ዋጋ ለፈረመው የምግብ ኮንትራት ተጠያቂ ናቸው በሚል ከተከሰሱ በኋላ ነው።
ሻፖቫሎቭ ክሱን "መሰረተ ቢስ " በማለት ውድቅ ቢያደርጉትም፤ ሚኒስቴሩ ግን የሻፖቫሎቭን መልቀቅ "የህብረተሰቡን እና የዓለም አቀፍ አጋሮችን እምነት የሚጠብቅ ጥሩ እርምጃ ነው" ብሎታል፡፡
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ኪሪሎ ቲሞሼንኮም ከሃላፊነታቸው ከለቀቁ ባለስልጠናት መካካል ይገኙበታል፡፡
የስራ መልቀቂያ ደብዳቤን ማስገባታቸው በማህበራዊ ሚዲያ ያስታወቁት ቲሞሼንኮ ፤ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ እስካሁን ለሰጧቸው እምነት እና እድል አመስግነዋል፡፡ የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊው በእጅ ጽፈው በለጠፉት ደብዳቤ ፤ በምን ምክንያት እንደለቀቁ ግን ያሉት ነገር የለም፡፡
ይሁን እንጅ ቲሞሼንኮ በስልጣን ዘመናቸው በተለያዩ ቅሌቶች ውስጥ መሳተፋቸው ይነገራል፡፡
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ ለዩክሬን የተበረከተ መኪና ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በተጨማሪም የዩክሬን ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኦሌክሲ ሲሞንኮ ግልጽ ባላደረጉት ምክንያት ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን አስታውቋል፡፡
ሲሞንኮ በቅርቡ በስፔን በነበራቸው የእረፍት ጊዜ ባለቤትነቱ የዩክሬን ቱጃር የሆነ መኪና ተጠቅመዋል የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ነው እየተነገረ ያለው፡፡
ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ሰኞ እለት ባደረጉት ንግግር ከስራ ጋር ላልተገናኙ ጉዳዮች ወደ ውጭ ሀገር የሚጓዙ ባለስልጣናትን ማገዳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
"አሁን ማረፍ ከፈለጉ ከመንግስት ስራ ውጭ ይረፉ። ከአሁን በኋላ ባለስልጣናት ለእረፍትም ሆነ ለሌላ መንግስታዊ ላልሆነ ዓላማ ወደ ውጭ ሀገር መሄድ አይችሉም" ሲሉም ነበር የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፡፡
ኬቭ ሁሉን አቀፍ የጸረ ሙስና እርምጃ እወስዳሁ ያለችው የዩክሬን የማህበረሰብ፣ የግዛት እና የመሰረተ ልማት ምክትል ሚኒስትሩ በገንዘብ ምዝበራ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነው።