ከአፍሪካ ጫፍ እስከ ጫፍ የሮጠው ብሪታንያዊ በኢትዮጵያ ምን ገጠመው?
በ301 ቀናት ውስጥ 9 ሀገራትን (10 ሺህ 973 ኪሎሜትር) ያቋረጠው የ57 አመት ጎልማሳ የአለም ክብረወሰንን ሰብሯል
ግለሰቡ ሩጫውን ያደረገው በአፍሪካ ድህነትን ለመቀነስ ለሚሰራ ግብረሰናይ ድርጅት ገንዘብ ለማሰባሰብ ነው
ትውልደ ደቡብ አፍሪካዊው የብሪታንያ ዜጋ አፍሪካን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመሮጥ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል።
ኬት ቦይድ የተባለው የ57 አመት ጎልማሳ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ግብጽ ድረስ 10 ሺህ 793 ኪሎሜትሮችን ሮጧል።
ሩጫውን ለማጠናቀቅ የወሰደበት 301 ቀንም ከዚህ ቀደም የአለም ክብረወሰን ሆኖ ከተመዘገብው በ17 ቀናት ይቀድማል ብሏል የአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ በድረ ገጹ ባወጣው ዘገባ።
ኬት ከደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ተነስቶ ቦትስዋና፣ ዚምባቡዌ፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ሱዳንን አዳርሶ ግብጽ ካይሮ ላይ ሩጫውን አጠናቋል።
ለ30 አመታት በአፍሪካ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ላይ የሰራው ጎልማሳው ሩጫውን ያደረገው “ሬይንቦው ሊደርስ” ለተሰኘ በአፍሪካ ድህነትን ለማስወገድና የምርጫ ተሳትፎን ለማበረታታት ለተቋቋመ ግብረሰናይ ድርጅት ገንዘብ ለማሰባሰብ ነበር።
ከባድ የአዕምሮና የአካላዊ ዝግጁነት የሚጠይቀውን ሩጫ ማጠናቀቅ አፍሪካውያን ወጣቶችን እንደሚያነሳሳ በማመን የጀመረውን ጉዞ በስኬት ለማጠናቀቅም በሳምንት 200 ኪሎሜትሮችን በመሮጥ ሲዘጋጅበት መቆየቱን ያወሳል።
በሱዳን ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ከካይሮ ሊጀምረው የነበረውን ሩጫ አቅጣጫ አስለውጦት ከኬፕ ታውን መነሻውን ያደረገው ኬት በኢትዮጵያ ግን ያልጠበቀው ፈተና እንደገጠመው ተናግሯል።
ደቡብ አፍሪካን በ47 ቀናት፤ ቦትስዋና እና ዚምባቡዌን ደግሞ በሁለት ሳምንታት በእግሩ ያቋረጠው ብሪታንያዊ፥ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያን ለማቋረጥ ሶስት ወራት የሚጠጋ ጊዜ ወስዶበታል።
በቀን በአማካይ 50 ኪሎሜትሮችን የሞሮጠው ኬት ኢትዮጵያ ስደርስ እስከመታገት የደረሰ ፈተና ገጠመኝ ይላል።
ኬት አማራ ክልል ሲደርስ ከኋላው መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ይዘውለት በተሽከርካሪ ከሚከተሉት የቡድን አጋሮቹ ጋር ሩጫውን ማድረግ እንደማይችል በታጠቁ ሃይሎች እንደተነገረው ከደቡብ አፍሪካው ኬፕቶክ ሬዲዮ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
ተመልሰው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሞክሩ ግን ታግተው 1 ሺህ ዶላር ከፍለው እንደተለቀቁም ያወሳል።
100 ኪሎሜትሮችን በመከላከያ ሰራዊት ታጅቦ መሮጥ መቻሉን በመግለጽም ከዚያ በኋላ መቀጠሉ አስጊ ሲሆንበት ወደ ሱዳን ማቅናቱን ይገልጻል።
በሱዳን ባለው ጦርነት ምክንያት በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ሩጫውን በማድረግ ወደ ግብጽ መሻገሩንም በማከል።
ከኬፕ ታውን ከተነሳ በ270ኛ ቀኑ ካይሮ የደረሰው የ57 አመት በጎፈቃደኛ፥ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ለመሻገር ቀሪ 500 ኪሎሜትሮችን ለመሮጥ የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎችን እንዲመድብለት ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘም አስታውሷል።
ከኬፕ ታውን እስከ ካይሮ (10 ሺህ 793 ኪሎሜትሮችን) የሮጠው ኬት ቦይድ በየሀገሩ የገጠመውን ፈተና የሚያትትበትን “ራኒንግ አፍሪካ” የተሰኘ መጽሃፍ እየጻፈ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው።