በአሜሪካ ያለጥፋታቸው ለ31 ዓመት ለታሰሩ ወንድማማቾች 84 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተሰጣቸው
ወንድማማቾቹ በፈረንጆቹ በ1983 የ11 ዓመት ሴት ልጅ አስገድዳችሁ ደፍራችኋል በሚል ነበር የታሰሩት
ሄንሪ ሊ ማክኮልምና ልዮን ብራወን የሚባሉት ወንድማማቾቹ ከ31 ዓመታት እስር በኋላ ከወንጀሉ ነጻ ተብለዋል
አፍሪካ አሜሪካዊ የሆኑት ሁለቱ ወንድማማቾች ባልሰሩት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው በሚል ለ31 ዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።
ወንድማማቾቹ ሄንሪ ሊ ማክኮልም እና ልዮን ብራውን ይባላሉ፤ መጠነኛ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለባቸውም ይነገራል።
ሁለቱ ወንድማማቾቾ በፈረንጆቹ 1983 ላይ ነበር የ11 ዓመት ሴት ልጅ አስገድዳችሁ ደፍራችኋል በሚል ለእስር የተዳረጉት።
ወንድማማቾቹ በወንጀሉ ተጠርጥረው ለእስር በተዳረጉበት ወቅት የ19 እና 15 ዓመት እድሜ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ ባልሰሩት ወንጀል በግድ እንዲፈርሙ መደረጋቸውንም ይናገራሉ።
ሆኖም ግን በፈረንጆች በ2014 በዘረ መል (ዲ.ኤን.ኤ) የተገኘ የምርመራ ውጤት የሁለቱን ወንድማማቾች ጥፋተኝነት የሚቀይር ሆኗል።
በምርመራውም ልጅቷ በተደፈረችበት ወቅት ሁለቱ ወንድማማቾች አጠገቧ እንዳልነበሩ እና በስፍራው የነበረው ሌላ ሰው እንደነበረ መለየት ተችሏል።
ይህንን ተከትሎም ሄንሪ ሊ ማክኮልም እና ግማሽ ወንድሙ ልዮን ብራውን በጉዳያቸው ላይ ይግባኝ የጠየቁ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን በመግለጽም ክስ ይከፍታሉ።
በዚህም መሰረት ባሳለፈወነው አርብ የተሰየመው ችሎት ለሁለቱ ወንድማማቾች 84 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ወስኖላቸዋል።
ለሁለቱ ወንድማማቾች የተወሰነው ካሳም በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሎለታል።