አሜሪካ “ካምፕ-7” የተባለውን ድብቅ የጓንታናሞ እስር ቤት ዘጋች
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጓንታሞን የመዝጋት እቅድ እንዳላቸው ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው
እስረኞቹ ኩባ ውስጥ ወደሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር መዛወራቸው ተገልጿል
የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣናት እንዳሉት ከሆነ በጓንታናሞ ውስጥ በአንድ ወቅት አሜሪካ እንደ ድብቅ እስርቤት ሰትጠቀምበት የነበረና ካምፕ-7 በመባል የሚታወቀው ክፍል መዝጋቷንና እስረኞቹ ኩባ ውስጥ ወደሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር መዛወራቸው ገልፀዋል፡
በካምፕ 7 የሚገኙ እስረኞች እንዲዛወሩ የተደረገው “የአፈፃፀም ቅልጥፍናን እና ውጤታማነትን ለማሳደግ” በሚል እሳቤ ነው ሲል የአሜሪካ የደቡብ እዝ መግለፁን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ በሚያሚ መቀመጫው ያደረገውና ኩባ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር በበላይነት የሚመራው እዙ፤ የተዛወሩትን እስረኞች ቁጥር ምን ያክል እንደሆነ ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡
እስረኞቹ ከካምፕ 7 ወደ ኩባው ካምፕ 5 ሲዛወሩ “ደህንነታቸው ተጠብቆና ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው እንደሆነም” ነው የደቡብ እዙ ያስታወቀው፡፡
የጓንታናሞው ካምፕ 7 በድብቅ ኔትወርክ ውስጥ ለተያዙ እስረኞች የእስር ማቆያ በሚል በፈረንጆቹ ታህሳስ 2006 በአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ተቋም (ሲ.አይ.ኤ ) አማካኝነት የተከፈተ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ጥቁሮች በግፍ ከሚሰቃዩባቸውና “የጥቁር ጣቢያዎች” ተብለው ከሚጠሩ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡
እናም አሁን የተደረገው ዝውውር በደቡብ እዙና በሲ.አይ.ኤ ስምመነት የተደረገ ነው ተብለዋል፡፡
ወታደራዊ ክንፉ የካምፕ-7 ትክክለኛ ቦታ ለማሳወቅ ለረዥም ጊዝያት ዳተኛ ሆኖና ለጋዜጠኞች ዝግ አድረጎ ቆይተዋል፡፡የፔንታጎን አለቆችም ቢሆኑ ካምፑ ከእድሳትና ግንባታ ጋር በተያያዘ ለውጦች ይደረጉበታል በማለት ሂደቱን ከማዘግየት በዘለለ እስካሁን በተግባር ጠብ የሚል ነገር ሲሰሩ አልተስተዋልም፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነም ቴድያ በካምፕ 7 ውስጥ ከነበሩት እስረኞች፤ አምስቱ ከመስከረም 11/2001ዱ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ አቅደዋል እንዲሁም የሎጂስቲከስ ድጋፍ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡
አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን የሀገሪቱ ኮንግረስ ካፀደቀላቸው ፤ እስረኞቹን ወደ አሜሪካ የማዛወርና ጓንታሞን የመዝጋት እቅድ እንዳላቸው ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡