አሜሪዊው ሚሊየነር እርጅናን ያስቀራል ያለውን ምርቱን መሸጥ ሊጀምር ነው
ብሪያን ጆንሰን የተባለው የቴክኖሎጂ ፈጣሪ የ"ጸረ እርጅና" ቀመሩን በ343 ዶላር በ23 ሀገራት ማቅረብ እጀምራለሁ ያለው
ሚሊየነሩ እድሜዬን በአምስት አመት ወደኋላ መመለስ ችያለው ማለቱ አነጋጋሪ ነበር
እርጅናን ማስቀረት እንደሚቻል ደጋግሞ በመናገር የሚታወቀው አሜሪካዊው የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ብሪያን ጆንሰን የጸረ እርጅና ቀመሩን ለገበያ ሊያውል መሆኑን ገልጿል።
ሚሊየነሩ ጆንሰን እርጅናን ታሪክ የሚያደርግ ነው ያለውን “ፕሮጀክት ብሉፕሪንት” የተሰኘ ፕሮግራም ማስተዋወቁ ይታወሳል።
ይህም ፕሮግራም ልዩ አመጋገብና በቀን ከ100 በላይ ደጋፊ ምግቦች (ሰፕልመንትስ) መጠቀምን የሚያዝና ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው።
የ“ፕሮጀክት ብሉፕሪንት” አካል የሆነው “ብሉፕሪንት ስታክ” የተባለ ምርትም ከነገ በስቲያ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል።
በመድሃኒት መልክ የተዘጋጀው “ጸረ እርጅና” ምርት የተለያዩ ፈሳሽ ውህዶች፣ ፕሮቲን፣ የእባብ ዘይትና ከ400 ካሎሪ በላይ ያካተተ እና ከ1 ሺህ ጊዜ በላይ በክሊኒክ ሙከራ የተደረገበት መሆኑ ተገልጿል።
ጆንሰን ረጅም ምርምርና ሙከራ ተደርጎበታል ያለውን ምርት በወር በ343 ዶላር ለሽያጭ ማቅረቡን አስታውቋል።
በይዘቱ “ከእናት ጡት ውጭ የሚወዳደረው የለም” ያለውን የምርምር ውጤት በ23 ሀገራት ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁንም ነው የገለጸው።
አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊዘርላንድ እና አረብ ኤምሬትስ “ብሉፕሪንትስ ስታክ” ከነገ በስቲያ ጀምሮ ከሚገኝባቸው ሀገራት መካከል ይገኙበታል።
የቀድሞው የሲልከን ቫሊ ስራ አስፈጻሚ እርጅናን ለማስቀረት በሚካሄዱ ምርምሮች መጠመዱ ይነገራል።
ጆንሰን በቅርቡም አመጋገብና እንቅስቃሴውን በማስተናከል ከእድሜው ላይ አምስት አመት መቀነስ መቻሉን መግለጹን ኤንዲቲቪ አስታውሷል።
በፕሮጀክት ብሉፕሪንት ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየሰራ ያለው ጆንሰን፥ ባለፈው አመትም በራሱ የምርምር ውጤት የጸጉር መበጣጠስ (መመለጥን) ማስቆም መቻሉን መናገሩ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ሚሊየነሩ የሚያነሳቸው ጉዳዮች በሳይንሳዊ መንገድ ውጤታማነታቸው አልተረጋገጠም።