የአፍሪካን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ የስራ ፈጣሪዎችን የዲጂታል አቅም ማነጽ አስፈላጊ መሆኑ ተገለፀ
አፍሪካውያን በእውቀት ላይ የተመረኮዘ “የማርኬቲንግ ስትራቴጂ” ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ኤ-ትሬድ ግሩፕ አስታውቋል
ኤ-ትሬድ ግሩፕ፡ የስልጠና ማእከሎችን በመክፈት ከ3 ሺህ በላይ ኢንተርፕረነሮች እያሰለጠነ መሆኑንም ገልጿል
ኤ-ትሬድ ግሩፕ (Ae Trade Group) የዲጂታል አቅምን በመጠቀም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ከድህንት አረንቋ እንዲወጡ የሚሰራ የማህበራዊ ድርጅት ነው።
ድርጂቱ ካለፈው አመት አንስቶ ከአህጉሪቱ ተቋም አፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር የአፍሪካውያን በተለይም በጥቃቅን እና አነስተኛ (Small businesses) የተሰማሩ ሴቶችና ወጣቶችን የዲጂታል አቅም በማነጽ ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ስዩም ለአል-ዐይን ኒውስ እንደተናገሩት፤ የአፍሪካውያን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ ስራ ፈጣሪዎችን በዲጂታል አቅም ማነጽ አስፈላጊ ነው።
ዋና ስራ አስፈጻሚው “ኤ-ትሬድ ግሩፕ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ሁሉን አቀፍና ዘለቂ በሆነ መልኩ የአፍሪካውያንን የዲጂታል አቅምን በማሳደግና ሊታይ የሚችል ለውጥ ለማምጣት እቅዶ እየሰራ ነው” ብለዋል።
የአፍሪካን ንግድ ዲጂታላይዝ ለማድረግ ኤ-ትሬድ ግሩፕ ከአፍሪካ ህብረት የመግባብያ ስምምነት ተፈራርሞ የተለያዩ ስራዎች ማከናወን መጀመራቸውንም ገልጸዋል።
“ንግድ እንዴት እንደሚሠራ ማሳወቅ፣ ተመጣጣኝ ፋይናነስ እና የንግድ ሎጂሰቲክሶች ኤ-ትሬድ ግሩፕ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር እየሰረባቸው ያሉ ቁልፍ ጉዳዮች መሆነቸውን” ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ሙሉዓለም ስዩም አስታውቀዋል።
አሁን ባለው የዲጂታል ዓለም ውስጥ በሁሉም ነገር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ማርኬቲንግ ስትራቴጂ መጠቀም የግድ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ኤ-ትሬዲንግ በአህጉሪቱ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የስልጠና ማእከል አዘጋጅቶ ስራ ፈጣሪዎችን ለማሰልጠን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።
“እስካሁን ከ3 ሺህ በላይ ስራ ፈጣሪዎች (ኢንተርፕሪነሮች)እያስተማርን እንገኛለን” ነው ያሉት።
አፍሪካውያን የዲጂታል አቅም ማሳደግ ከቻሉ የአፍሪካ ምርቶች ከአፍሪካ አልፈው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የማሆኑበት ምክንያት የለም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ የአፍሪካ መንግስታት የተሸለ የማርኬቲንግ ስትራቴጂ በመከተል ረገድ በትኩረት ቢሰሩ ሲሉም ጠይቋል።