በኢትዮጵያ ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ግንባታቸው መቆሙ ተገለፀ
የሆቴሎቹ ግንባታ የቆመው በውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በባለሀባቶች ፍላጎት ማጣት ነው ተብሏል
ለገና በዓል ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ የተባሉት ዳያስፖራዎች የሁቴል ኢንዱስትሪውን እንደሚያነቃቃው ተገልጿል
በኢትዮጵያ ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ግንባታቸው መቆሙ ተገለ።
የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን መከሰቱን ተከትሎ እንቅስቃሴ ገደቦች በመጣላቸው ክፉኛ ከተጎዱት ውስጥ የሆቴል ኢንዱስትሪ አንዱ ነው።
የኮሮና ቫይረስ ጉዳት ባልቆመበት ሁኔታም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥረቶች በየአካባው በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንትም የሆቴል ኢንዱስትሪ በመፈተን ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት አሰሪዎች ፌደሬሽን አስታውቋል፡፡
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር) ለአል-ዐይን አማርኛ እንዳሉት፤ የሆቴል ኢንዱስትሪ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳት እንዲያገግም ለመንግስት በቀረቡለት ምክረ ሀሳቦች መሰረት እርምጃ መውሰዱ ዘርፉን ከባሰ ጉዳት ታድጎታል ብለዋል።
የኮቪድ ፕሮቶኮል በሚል ወደ ስራ የተተገበረው አሰራር በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስራ አቁመው የነበሩ ሆቴሎችን ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረጉን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የብድር አገልግሎት እና ሌሎች ለሆቴል ኢንዱስትሪው አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች ተወስነው ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አፈጻጸሙ ላይ ችግሮች እንደነበሩም አክለዋል።
ሆቴሎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በአንድ ዓመት ውስጥ የምንመልሰው ብድር በብሄራዊ ባንክ ትዕዛዝ ከባንኮች ተመቻችቶልን ነበር ነገር ግን ኮቪድ አሁንም ስላለ እና ጉዳቱ ስለቀጠለ ብድር የመመለሻ ጊዜውን ለ5 ዓመት እንዲራዘም መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
አሁን “የኮቪድ ጉዳት እንዳለ ሆኖ ጦርነቱ በሁለት መንገድ እየጎዳን ነው፤ አንደኛ በጦርነቱ ሆቴሎች እየወደሙ እና ከስራ ውጪ መሆናቸው ሲሆን ሁለተኛው አሜሪካን ጨምሮ ብዙ የምዕራባዊያን አገራት ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸው እና በዚህ ምክንያት ሁነቶች እየቀነሱ ነው” ይህ መሆኑ ደግሞ የሆቴል ቢዝነሱን እየጎዳው መሆኑን ፕሬዘዳንቱ ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጦርነቱ ማህበራዊ መስተጋብራችንን የጎዳውን ያህል የከፋ የኢኮኖሚ ጉዳት ሳያደርስ መንግስት እርምጃ እንዲወስድም ፕሬዘዳንቱ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ እድገት ጥሩ የሚባል ነው የሚሉት ፕሬዘዳንቱ አሁን ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ግንባታቸው መቆሙን ተናግረዋል።
እንደ ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር) ገለጻ “የነዚህ ሆቴሎች ግንባታ የቆመው በውጭ ምንዛሬ እና በባለሃብቶች ፍላጎት ማጣት ምክንያት ነወ”።
ይህ በዚህ እንዳለ ሆኖ የሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሪፎረም መደረግ እያለበትም ቢሆን ተስፋ ሰጪ ዘርፍ ነው። በየዓመቱ እያሳየ ያለው እድገትም ጥሩ የሚባል መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ሁሉም ሆቴሎች በኢትዮጵያውያን መያዙ ትልቁ ነገር ነው የሚሉት ዶክተር ፍትህ፤ መንግስት ለዚህ ዘርፍ ድጋፎችን ማደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
አሁን ላይ በስራ ላይ ያሉት አብዛኞቹ ሆቴሎች ከ10 እና 15 ዓመታት በፊት በመንግስት የተለያዩ ማበረታቻዎች የተገነቡ ናቸው የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ የባንክ እዳቸውን በዚህ ጊዜ ማጠናቀቅ ያለባቸው ቢሆንም ላለፉት 5 ዓመታት ያለፍንበት የፖለቲካ ሁኔታ ሆቴሎቹ ብድራቸውን አጠቃለው መክፈል በሚችሉበት ቁመና ላይ አይደሉምም ብለዋል።
በመሆኑም እነዚህ ሆቴሎች የተበደሩት ብድር የተበላሸ ብድር ሆኖ ከመመዝገባቸው በፊት መንግስት የብድር ማራዘሚያ ውሳኔዎችን ቢወስን ዘርፉን ከውድቀት እና አገር ላይ ሊደርስ የሚችለውና ጉዳት ይታደገዋል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ የሆቴሎች አገልግሎት ክፍያ ውድ የሚሆነው እነዚህ ሆቴሎች ያለባቸውን ብድር የግድ በ10 እና 15 ዓመት መክፈል ስላለባቸው ነውም ብለዋል።
ሆቴሎች አገልግሎቶችን በውድ ዋጋ በሰጡ ቁጥር ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አገራት ሁነቶችን ከአዲስ አበባ ውጭ ለማካሄድ ይገደዳሉ፤ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሆቴሎችን ተወዳዳሪነት ከመጉዳት ባሻገር ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ የኮንፈረንስ ቱሪስቶችን ቁጥር በመቀነስ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ይቀንሳል፣ የብድር መክፈያ ጊዜው ቢራዘም እነዚህ ሁሉ ጉዳቶች ይቀንሳል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ብዙ የሚገበኙ ታሪካው ቦታዎች እና ቅርሶች በመኖራቸው ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች ከስራ ውጪ ሆነዋል።
በጦርነቱ ምን ያህል ሆቴሎች ወድመዋል? በሚል የተጠየቁት ዶክተር ፍትህ “ጦርነቱ አሁንም የቀጠለ በመሆኑ የተደራጀ መረጃ የለንም” ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ መደረጉ የሆቴሉን ኢንዱስትሪ እንደሚያነቃቃውም ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል።
የሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪዎች ለነዚህ ወገኖች የ30 በመቶ ቅናሽ እናደርጋለን የሚሉት ፕሬዘዳንቱ፤ በአጭር ቀናት ውስጥ አንድ ሚሊዮኑ ዳያስፖራዎች ይመጣሉ ብለን ባይጠበቅም በተመቻቸው ጊዜ ይምጡ ቅናሽ አድርገን እንጠብቃቸዋልን ሲሉ አክለዋል።