የቡልጋሪያው እግርኳስ ክለብ ለቀድሞ ኮከቡ በስህተት የህሊና ጸሎት አድርጓል
ስታዲየም ውስጥ የህሊና ጸሎት የተደረገለት ተጫዋች ሞቱን በቴሌቪዥን ከተመለከተችው ሚስቱ ሰምቷል

አርዳ የተሰኘው ክለብ በተሳሳተ መረጃ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቋል
በብልጋርያ የመጀመሪያ ዲቪዚዮን የሚጫወት ክለብ በህይወት ላለ የቀድሞ ኮከብ ተጫዋቹ የህሊና ጸሎት አድርጓል።
አርዳ ካርዛሊ የተሰኘው ቡድን የሊግ ተቀናቃኙን ሌቭስኪ ሶፊያ ባለፈው እሁድ ሲገጥም ነው አስገራሚው ክስተት የተፈጠረው።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች በሜዳው መሀል ላይ ተሰባስበው ለአርዳ ክለብ የቀድሞ ኮከብ ተጫዋቹ ፔትኮ ጋንቼቭ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ክለቡ የቀድሞ ተጫዋቹን ለመልካም ግልጋሎቱ ክብር ለመስጠት ያደረገው ነገር በስህተት የተፈጸመ መሆኑን ከረፈደም ቢሆን ተረድቷል።
ጨዋታው መካሄዱ እንደቀጠለ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይቅርታ ጠይቋል።
"ለቀድሞው ተጫዋቻችን ፔትኮ ጋንቼቭ እና ለቤተሰቦቹ ታላቅ ይቅርታ ያደርጉልን ዘንድ እንጠይቃለን፤ ክለቡ ስለተጫዋቹ ህልፈት ያገኘው መረጃ የተሳሳተ ስለነበር ነው" የሚል መግለጫን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል።
የቀድሞ ኮከቡ ረጅም እድሜ ተሰጥቶት የክለቡን ስኬት ይመለከት ዘንድም ተመኝቷል።
በቴሌቪዥን ጨዋታውን ስትመለከት የፔትኮን ህልፈት የተረዳችው ሚስቱ ከባድ ድንጋጤ ውስጥ እንደገባች ተናግራለች።
የአርዳ ክለብ ጨዋታ የማያልፈው ባሏ ጨዋታው ከተጀመረ 10 ደቂቃዎች ቢቆጠሩም ወደቤቱ አለመመለሱም ስጋቷን ይበልጥ እንደጨመረው ታወሳለች።
"እንደተመለስኩ ባለቤቴ በእምባ ተቀበለችኝ" የሚለው የቀድሞው ተጫዋች፥ "ፔትኮ ፔትኮ በቴሌቪዥን እኮ መሞትክን ተናገሩ፤ ምን እያሉ እንደነበር እና ምን እንደተፈጠረ ሊገባኝ አልቻለም" በማለት በሲቃ ውስጥ ትናገር እንደነበር ቢቲቪ ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ገልጿል።
በስራ ምክንያት ባይዘገይ ኖሮ የራሱን የህልፈት መርዶ በቴሌቪዥን ይመለከት እንደነበርም ነው የተናገረው።
ክለቡ እንዴት እንዲህ አይነት ከባድ ስህተት ይሰራል ያሉ ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እያጋሩ ነው።
ተጫዋቹ በህይወት መኖሩ ትልቅ ነገር ነው ያሉት ደግሞ በቀጣይ ሳምንት የህሊና ጸሎት ሳይሆን የአንድ ደቂቃ የአድናቆት ጭብጨባ እንዲደረግለት ጥሪ አቅርበዋል።